ወጣቶችን ከአደንዛዥ ዕጽ ተጋላጭነት ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት ሊደረግ ይገባል

85
ጅማ 27/2010 ወጣቶችን ከአደንዛዥ ዕጽ ተጋላጭነት ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስገነዘበ። ባለስልጣኑ ዓለም አቀፍ የጸረ አደንዛዥ ዕጽ ቀንን በማስመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ትናንት በጅማ ከተማ አካሂዷል። የባለስልጣኑ  የማህበራዊ አገልግሎትና የጤና ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ  በቀለ ሰንበታ በመድረኩ ላይ እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት በከተሞች አደንዛዥ እጽን በመርፌ የሚወሰዱ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። "ይህ ደግሞ ወጣቱ ጥንቃቄ ለጎደለው የወሲብ ግንኙነትና ለወንጀል ድርጊት እየገፋፋው ስለሆነ ችግሩን ለመከላከል ህብረተሰቡ ትኩረት ሰጥቶ በቅንጅት ሊንቀሰቀስ ይገባል" ብለዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ንጉሴ ደያስ በበኩላቸው "አደገኛ ዕጽን የሚጠቀሙ ወጣቶች  ለኤች. አይ.ቪ፣ ለጉበትና ለሌሎችም ተላላፊ በሸታዎች የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው"ብለዋል። የአደንዛዥ እጽ ተጋላጭነት በአዲስ አበበና ሃዋሳ ከተሞች ጎልቶ እንደሚታይ በጥናት መረጋገጡን የጠቆሙት መምህሩ፣ በሃዋሳ ከተማ ብቻ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 7 መቶ የሚሆኑት አደገኛ እጽን በመርፌ ይወስዷሉ። "ከእነዚህ ዕጽ ተጠቃሚዎች መካከል 39 በመቶ የሚሆኑ ደግሞ የኤች. አይ. ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ እንዲሚገኝ ያረጋገጡ ናቸው" ብለዋል። እንደ ዶክተር ንጉሴ ገለጻ ዕጾቹን አንድ ጊዜ ለመጠቀም እስከ 140 ብር በአማካኝ የሚከፍል ሲሆን አንድ መርፌን አምስትና ከዚያ በላይ ወጣቶች በጋራ እንደሚጠቀሙ በአዲስ አበባና በሃዋሳ በተደረጉ ጥናቶች ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ  የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ  ቅርጫፍ ጽህፍት ቤት ኃለፊ አቶ አድናን ሻሚል በአደንዛዥ ዕጽ ለጉዳት የተጋለጠን ሰው ወደ ቀድሞው ጤንነት ለመመለስ አዳጋች በመሆኑ አስቀድሞ በመከላከሉ ሥራ ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል። በተለይ በመርፌ የሚወሰዱ እጾች ሱስ የማስያዝ አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ዜጎች አንዴ በሱስ ከተጠቁ በኋላ ወደ ጤነኛ ሕይወት ለመመለስ የረጅም ጊዜ ሕክምናና ውድ መድህኒቶች እንደሚስፈልጋቸው ተናግረዋል። አደንዛዥ እጽ በአካላዊና በስነልቦና ጤና ላይ ጉዳት ከማድረሱም በላይ ለወንጅል መስፋፋት ምክንያት በመሆኑ ሕብረተሰቡ ለጉዳዩ ክብደት በመስጠት ለመፍትሄው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የችግሩ ሰለባ የነበሩና በዓለም አቀፍ የጸረ አደንዛዥ ዕጽ ቀን መድረክ  ላይ በመገኘት ተሞክራቸውን ያካፈሉ  አንድ ግለሰብ በበኩላቸው እንዳሉት ሱስኝነት እራሱን የቻለ ህመም ነው። "ተጠቂዎችን እንደ ወንጃለኛ በመቅጣትና ከህብረተሰቡ እንዲገለሉ ማድረግ ችግሩን የሚያቃልለው ባለመሆኑ በቅርበት ሆኖ መርዳት የገቢ ነው" ብለዋል። "በከባድ ሱስ የተጠቁ ህጻናትና ወጣቶችን ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ከቅጣት ልናድናቸው ይገባል" ያሉት ግለሰቡ በተለይ ወጣቶች በብዛት በሚገኙበት የትምህርት ተቋማት አካባቢዎች አደገኛ እጾች ለገበያ እንዳይቀርቡ የመከላከል ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ሰሚራ ሀሰን በበኩሏ በሱስ የተጠቁ ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከመስራት ይልቅ መቅረብና ማድመጥ እንዲሁም ከችግሩ የሚወጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ መሆኑን ገልጻለች። በመድረኩ ላይ ከጅማ ከተማ የተውጣጡ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም