የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የሎጀስቲክስ አገልግሎት አቅም ማጎልበቱ ተገለጸ

94
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር በጅቡቲ ወደብ የተከማቹ ኮንቴይኔሮችን ለማመላለስ የሎጀስቲክስ አገልግሎት አቅሙን እንዳሳደገለት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ። በጅቡቲ ወደብ የተከማቹ የኢትዮጵያ ኮንቴይነሮች አገሪቱን ለከፍተኛ ወጭ እየዳረጓት ያሉና በወደቡ የሚታየውም መጨናነቅ ችግር አለመቀረፉን ከሰሞኑ የትራንስፖረት ሚኒስቴር የ11 ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተመልክቶ ነበር። በሪፓርት ግምገማው መሰረትም በወደብ ላይ ያለው የዕቃ ክምችት ኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ አገልግሎት ያላትን ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዳታሻሽል ማድረጉ ተገልጿል። የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖረትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በበኩሉ ችግሩን ለማቃለል የኢትዮ-ጅቡቲ የምደር ባቡር ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጿል። በድርጅቱ የወደቦችና ፋሲሊቲ ዳይሬክተር ኢንጂነር አሰፋ ወርቅነህ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ድርጅቱ ሁለት ኮንቴነሮችን በሚይዝ ተሽከርካሪ ያመላልስ ከነበረበት አሁን ላይ በአንድ ጊዜ 106 ኮንቴይነሮችን በባቡር አጓጉዞ ሞጆ ደረቅ ወደብ እያደረሰ ነው። ይህም በጅቡቲ ከልክ በላይ ለተፈጠረው የኮንቴይኔር ክምችትን ለመቅረፍ እያገዘ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ድርጅቱ ወደፊት በድሬዳዋና ኮምቦልቻ ደረቅ ወደቦች በባቡር የሎጂስቲክስ አገልገሎቱን ለማሳለጥ በጥናትና ግንባታ ላይ መሆኑን አንስተዋል። የደረቅ ወደብ አገልግሎት የባሕር ወደብ ለሌላት ኢትዮጵያ "የባህር ወደብ አገልግሎቱን የሚተካ ነው" የሚሉት ደግሞ በድርጅቱ የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ጉቱ ናቸው፤ እንደሳቸው ገለጻ ድርጅቱ ደረቅ ወደቦችን በተለያዩ የልማት ኮሪደሮች የመገንባቱን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል።  በሌላ በኩል ደርጅቱ በኤክፖርት መስክ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የኤክስፖርት ስራዎችን በኮንቴይኔር በመላክ የውጭ ምንዛሬ ወጭና የሚደርሰውን ብክነት ለመቀነስ የተለያዩ ማበረታቻዎች እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም