ህብረተሰቡ ኮሮናን ለመከላከል ምክሮችንና መመሪያዎችን ማክበር አለበት... ሰግለን ኢሉ አባ ገዳ

58

መቱ ፣ ሚያዝያ 22/2012 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቋቋሙ ግብረሃይል መመሪያና የባለሙያዎችን ምክር በመተግበር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ በሰግለን ኢሉ የመቱ አባገዳ አሳሰቡ ።

የቫይረሱን አሳሳቢነት ተገንዝቦ መመሪያውን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በህብረተሰቡ አልፎ አልፎ ቸልተኝነት እንደሚታይ ደግሞ አንዳንድ የመቱ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል::

የሰግለን ኢሉ አባገዳዎች ጉባኤ አባልና የመቱ አባገዳ ተሰማ ሙሉነህ እንዳሉት ቫይረሱ በአደጉት አገራት እያመጣ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመረዳት ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት::


"ማህበራዊ ርቀትን በመጠበቅና የእርስ በርስ ንክኪን የማስቀረት ጥንቃቄ በተለይ ወጣቶች ጋር አይስተዋልም" ያሉት አባ ገዳው ወጣቶች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል::


በተለይም በገበያ፣ በትራንስፖርት፡ በመንግስት መስርያ ቤቶችና በተለያዩ አገልግሎት መስጫ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ርቀቱን ሊጠብቅ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የህክምና ቴክኖሎጂዎችን በከፍተኛ ደረጃ ያሟሉ ያደጉ አገራት የገጠማቸውን ፈተና በመገንዘብ ህብረተሰቡ ለቅድመ ጥንቃቄው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም መክረዋል ።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በየደረጃው የተቋቋሙ ግብረሃይሎችና የጤና ባለሙያዎችም ተከታታይ ትምህርት ሊሰጡ እንደሚገባ የገለጹት አባ ገዳው  ህብረተሰቡ ለምክርና ለመመሪያው ተገዥ መሆን አለበት ብለዋል።  

በዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል የበጎ ፈቃድ ግንዛቤ ማስጨበጥ ኮሚቴ አባል ወጣት በኃይሉ ታምሩ እንዳለው በዞኑ 13 ወረዳዎች ከ4 ሺህ በላይ ወጣቶች ተሰማርተው በየመንገዱና ቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እያከናወኑ ነው:።

በመቱ ከተማ ቆሎ ኮርማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዮናስ ተፈራ እንዳሉት ለህብረተሰቡ በየወቅቱ ትምህርት እየተሰጠ ቢሆንም በግብይት ወቅት አሁንም ቸልተኝነት እንደሚስተዋል ተናግረዋል

ቫይረሱ አንድ ጊዜ ከተስፋፋ ከፍተኛ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ ህብረተሰቡ ከማህበራዊ ንክኪ ሊቆጠብ ይገባል ብለዋል ።

በተለይም በወጣቱ በቡድን የመጓዝና ርቀትን ያለመጠበቅ ሁኔታዎች አሁንም አልፎ አልፎ እንደሚስተዋል የተናገሩት ሌላኛዋ የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ ማርታ ብሩ፤ ቸልተኘነቱ ለጉዳት እንዳይዳርገን መጠንቀቅ ይበጃል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም