ኢትዮጵያውያን በጎነታችንን በተግባር ማሳየት ያለብን ጊዜ ላይ ነን... በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማሩ

72

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 22/2012 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያውያን የመረዳዳትና የመደጋገፍ መልካም ባህላችንን አሁን ላይ በተግባር ልናሳይ ይገባል" ሲሉ በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።

ኢዜአ በኢትዮጵያውያን እርስ በርስ የመተሳሰብ ልማድ ዙሪያ ከአርቲስት ሰለሞን ቦጋለ፣ ዶክተር በረከት አፈወርቅና ወይዘሮ ፈቲያ ሙሃመድ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበትን የመረዳዳትና የመደጋገፍ፣ ችግሮችን አብሮ የመፍታት ባህል ከመናገር በላይ በተግባር የሚያሳዩበት ጊዜ አሁን መሆኑንም ተናግረዋል።

"በአንድ አጋጣሚ ጎረቤት ስንጠይቅ አራት ሺህ በማይሞላ ብር ችግር ስድስት አመት በአልጋ ላይ የቆየ ታማሚ አጋጥሞኛል" ያለው አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ፤ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ጎረቤትን መጠየቅና መደገፍ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

''ጎረቤትን የመርዳት ባህላችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል'' ሲልም ተናግሯል።

በሞዴሊንግ ሙያ ዘርፍ ተሰማርታ የምትገኘው ወይዘሮ ፈቲያ መሃመድ "ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀው አብሮ በመብላትና በመረዳዳት ነው" ብላለች።

ይህንን መታወቂያ በአሁኑ ወቅት ይበልጥ በማዳበር ችግርን ለማለፍ ማዋል እንደሚገባ ገልጻለች።

የጎረቤት መጠያየቅና የበጎነት ባህሉ ጎልቶ መታየት ያለበት ጊዜ አሁን እንደሆነም ተናግራለች።

በቢሾፍቱ አየር ሃይል ሆስፒታል እያገለገሉ ያሉት ዶክተር በረከት አፈወርቅ በበኩላቸው ''በጎነት በመስጠት ብቻ ሳይሆን የሰውን ችግር እንደራስ አድርጎ መረዳት ጭምር ነው'' ብለዋል።

በመሆኑም ሁሉም ሰው በሙያውና ባለው የኢኮኖሚና የእውቀት ሃብት ከልብ ሆኖ ከሰራ ማናቸውንም ችግሮች ማለፍ እንደሚቻልም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በተወሰደው ርምጃ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከመንግስት ጎን በመሆን ድጋፋቸውን እያደረጉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም