የወሰን ማስከበር ሥራ ለመንገድ ፕሮጀክቶች መዘግየት ቁልፍ ተግዳሮት እየሆነ ነው

87
ሀዋሳ ሚያዚያ 30/2010 የወሰን ማስከበር ሥራ ለመንገድ ፕሮጀክቶች መዘግየት ቁልፍ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ግርማይ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሁን ወቅት ከ700 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረቶች ቢደረጉም የሚያጋጥሙ የተለያዩ ተግዳሮቶች በሥራው ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አርአያ ገለጻ ከአምስት ዓመታት በፊት በተጠና ጥናት አብዛኞቹ የመንገድ ፕሮጀክቶች ይዘገዩ የነበሩት በዲዛይን ለውጥ ምክንያት ነው፡፡ ለዚህም በፕሮጀክቶቹ ዲዛይን ላይ መመሪያዎችንና ጥናቶችን በማዘጋጀትና በማማከር በአሁኑ ወቅት ችግሮቹን መቀነስ አንደተቻለ አመልክተዋል፡፡ "በዚህ ምክንያት በመንገድ ግንባታ ሥራ ሊፈጠር የሚችላውን መዘግየትና የዋጋ ጭማሪ እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል" ያሉት አቶ አርአያ ችግሮቹ በከተሞች አካባቢ ጎልተው ይታዩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህ የወሰን ማስከበር ሥራዎች የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ለፕሮጀክቶች መዘግየት ቁልፍ ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ለዚህም የወሰን ማስከበር ሥራዎች በጊዜ አለመከናወናቸው በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡ የወሰን ማስከበር ሥራው ከካሳ ክፍያ ስርዓቱ ጀምሮ ግብዓት የሚቀርብባቸውን ቦታዎች እስከመለየት የሚደርስ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ ችግሩን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጀምሮ በአብዛኛው የየአካባቢው መስተዳደሮችና ባለድርሻ አካላት የሚፈጥሩት እንደሆነ ጠቁመው፣ "ችግሮቹ አስቀድመው በሚፈቱበት አካባቢ ፕሮጀክቶቹ አይዘገዩም" ብለዋል፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባዬ ገዛኸኝ በበኩላቸው ሕብረተሰቡ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በእኔነት ስሜት እንዲጠብቅ ግንዛቤ መፈጠር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ የምክር ቤት አባላት በተለያዩ ጊዜያት የመስክ ምልከታ እንደሚያደርጉ የገለጹት ወይዘሮ አበባዬ፣ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያየዞ የሚነሳው ችግር ተቀናጅቶ ባለመስራት የሚፈጠር እንደሆነም መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ ወይዘሮ አበባዬ እንዳሉት የኮንትራክተሮችን አቅም የማጎልበት ሥራ እና በመዘግየት ምክንያት ሊባክን የሚችለውን ሃብት ማዳን በቀጣይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል፡፡ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በበኩላቸው "በድርጅቱ እየተገነባ ያለው ከሞሮቾ ዲሚቱ ያለው 60 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሥራ በሰኔ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ይጠናቀቃል" ብለዋል፡፡ መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከተያዘለት ጊዜ በተወሰነ ደረጃ መዘግየቱን ገልጸው፣ የወሰን ማስከበርና በአካባቢው የዝናብ መብዛት ለመዘግየቱ ምክንያቶች እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፣ መንገዱ አንድ ቢሊዮን የሚጠገ ገንዘብ የፈጀ ሲሆን እስካሁንም አንድ ሺህ ለሚደርሱ የአካባቢው ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከሃዋሳ-ጩኮ እና ከሞሮቾ - ዲሚቱ - ሶዶ ያለውን የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሰሞኑን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተዘዋውሮ መጎብኘቱን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም