የተጓተተውን የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

61
ድሬደዋ ሰኔ 27/2010 ግንባታው ከ353 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተጀምሮ የተጓተተውን የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እንደሚሰራ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ። የድሬዳዋ ነዋሪች በበኩላቸው ግንባታው ለዓመታት የተጓተተው ሆስፒታል ለአገልግሎት የሚበቃበትን ቀን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡ የድሬዳዋ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በግንቦት 2002 ዓ.ም የተጀመረውና በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል የተባለው ሆስፒታል እስከዛሬ ድረስ ሳይጠናቀቅ ቆይቷል፡፡ በተለያየ ጊዜ የተደረገው የዲዛይን ለውጥና የጨረታ ሂደት መጓተት፣ የአማካሪ ድርጅቶች መለዋወጥ፣ ሥራ ተቋራጩ መሞትን ተከትሎ በፍርድ ቤት የይገባኛል ክርከር መነሳት ለግንባታው መጓተት በምክንያትነት ሆነዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ችግር፣ የሕንጻው ግንባታ ሥራው በሦስት የሥራ ተቋራጮች መከናወን የአቅም ውስንነቶች ለግንባታው መጓተት ተጨማሪ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ዶክተር ሙሉቀን አስረድተዋል፡፡ የሥራ ተቋራጮች በራሳቸው ለፈጠሩት ክፍተት በውሉ መሰረት ተገቢውን ቅጣት መቀጣታቸውን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት የዋና ህንጻ ግንባታ ሥራ 60 በመቶ መድረሱንና የማጠናቀቂያ ሥራውም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የህንጻው የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራና ተከላ ሥራው 98 በመቶ መድረሱን የገለጹት ዶክተር ሙሉቀን ለምድር ግቢ ግንባታ ሥራ ከውጭ የሚገቡ ቁሶች ከተሟሉ ሥራውን በቀላሉ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ለግንባታው የሚያስፈልጉና በውጭ ምንዛሬ ለሚገዙ ቁሶች መፍትሄ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ከተሳካ ሆስፒታሉ በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ የድሬዳዋ ጤና ጥበቃ ቢሮ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ቦጋለ ሰይፉ በበኩላቸው ህንጻው በመጀመሪያ በነባሩ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ለመገንባት በታቀደው መሰረት የዲዛይን ሥራው ተጠናቆ የመሰረት ሥራ ተጀምሮ እንደነበር  አስታውሰዋል። በሂደት ህንጻው በአዲስ ገቢ ራሱን ችሎ እንዲገነባ ሲደረገ ከዲዛይን ለውጥ በተጨማሪ ግንባታው ለሌላ ሥራ ተቋራጭ በጨረታ መሰጠቱን አመልክተዋል። የተሻሻለው የህንጻው ዲዛይን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲዋሀድ ለማድረግ ሲባል የማቀዝቀዣ፣ የኦክሲጂን፣ የቦይለር፣ የላውንደሪ፣ የማብሰያና መሰል የኤሌክትሮ መካኒካ ክፍሎች እንዲኖሩት መደረጉ ተጨማሪ 72 ሚሊዮን ብር መጠየቁንና ጨረታውም ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁን ተናግረዋል፡፡ የሆስፒታሉ  ምድረ ግቢ ለማሳመርና መሰረት ልማቶችን ለማሟላትም  በ61 ሚሊዮን ብር በ2007 ዓ.ም በሌላ ሦስተኛ የሥራ ተቋራጭ ሥራው መጀመሩን ኢንጂነር ቦጋለ ጠቁመዋል፡፡ እንደ ኢንጂነር ቦጋለ ገለጻ እነዚህ የምድረ ግቢና የኤልክትሮ መካካል ተከላ ሥራዎች  ከዋናው ህንጻ ንድፍ ጋር ተዋህደው አስቀድመው ቢዘጋጁ ኑሮ አስተዳደሩ ከጊዜና ከተጨማሪ ወጪ ይድን እንደነበር አመልክተዋል። ሆስፒታሉ በሚገነባበት የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር አቅራቢያ የሚኖሩት ወይዘሮ ዘሐራ ሐሰን በበኩላቸው ሆስፒታሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚጀምርበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ “ ግንባታው ከተጀመረ በኋላ በጣም ተጓቷል፤ ሠራተኞች ሁልጊዜም ሲሰሩ አያለሁ ፤ ነገር ግን እስከዛሬ ያልተጠናቀቀበት ምክንያት አልገባኝም ” ብለዋል፡፡ “ሆስፒታሉ ለድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ለምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ጭምር አግልግሎት መስጠት የሚያስችል ስለሚሆን ከወዲሁ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ትምህርት ጋር ማቆራኘት ቢቻል የተሻለ ጥቅም ይሰጣል” ያሉት ደግሞ የጤና ባለሙያው አቶ ብርሃኑ አበበ ናቸው፡፡ “ሆስፒታሉ በአካባቢያችን መገንባቱ ጥሩ ነው፤ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ተጉዘን ድል ጮራ ሆስፒታል ከመታከም ይታደገናል፤ የቀበሌው ነዋሪዎች የሆስፒታሉን መጠናቀቅ በጉጉት ነው እየተጠባበቅን ያለነው” ያሉት ደግሞ የመልካ ጀብዱ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መላኩ መልካ ናቸው፡፡ 130 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለውና በ4 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ እየተገነባ የሚገኘው የድሬዳዋ  ሪፈራል ሆስፒታል ሲጠናቀቅ 300 አልጋ ያላቸው መኝታ ክፍሎች እንደሚኖሩት ተገልጿል። ከእዚህ በተጨማሪም ተመላላሽ የሕክምና መስጫ እንዲሁም 11 የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ያሉት ሲሆን ለውስጥ ደዌ ሕክምና፣ ለህጻናት፣ ለመድኃኒት መሸጫ፣ ለድንገተኛ ሕክምና፣ ለላቦራቶሪና ለተለያዩ የሕከምና አገልግሎት መስጫ ክፍሎች እንደሚኖሩት የዘገበው ኢዜአ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም