የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚንስትር ፊልሰን አብዱላሂ በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ዜጎችን ጎበኙ

75

አዲስ አበባ ሚያዚያ  20/2012(ኢዜአ) የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚንስትር ፊልሰን አብዱላሂ በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ዜጎችን ጎበኙ።

በለይቶ ማቆያ ለሚገኙት ዜጎች የስነልቦና አማካሪዎች በበቂ ሁኔታ እንዲኖሩ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል። 

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚንስትር ፊልሰን አብዱላሂ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ የሚገኘውን ከስደት ተመላሾች ለይቶ ማቆያ ጎብኝተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ለይቶ ማቆያ በአሁኑ ወቅት 559 ከስደት ተመላሾች ሲኖሩ ከእነዚህ መካከል 133ቱ ህፃናት ናቸው።

በማዕከሉ የስነ ልቦና አማካሪ ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው በማቆያ ያሉትን በሙሉ በቅርበት ማማከር አልተቻለም።

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት የስነልቦና እና ማህበራዊ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥር ከፍ ለማደረግ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።

የለይቶ ማቆያ ማዕከሉ አስተባባሪ ዶክተር ቅድስት ገብረሃና እንዳሉት በማዕከሉ ውስጥ የአዕምሮ ህሙማን፣ ነብሰጡሮች አንዲሁም  133 ህፃናት ይገኛሉ።  

በማዕከሉ ለሚገኙ ከስደት ተመላሾች 31 የጤና ባለሙያዎች የህክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከስደት ተመላሾቹ መካከል የተለያዩ ችግሮችን የተጋፈጡና እስር ቤትም የነበሩ ስላሉ የስነ ልቦና ችግር ይስተዋልባቸዋል።

ለዚህም የስነልቦና እና ማህበራዊ ማማከር የሚሰጡ የሶሻል ወርክ ባለሙያዎች የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በማዕከሉ የሚገኙት 3 ባለሙያዎች ብቻ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በመሰል ለይቶ ማቆያዎች አገልግሎቶችን እየሰጠና ከስደት ተመላሾችን እየደገፈ መሆኑን ያስረዱት ደግሞ የድርጅቱ የስደትና ድንበር አስተዳደር መርሃግብር አስተባባሪ ሚስተር ሁጎ ጌነስት ናቸው።

በዛሬው እለት የሴቶች፣ ህፃናት ወጣቶች ሚኒስትር እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ተወካይ በማእከሉ ጉብኝት አድርገዋል።

ጉብኝቱ በተለይ ከስደት ተመላሽ ህፃናት በስደት ላይ የገጠሟቸውን ችግሮችና የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች ለእነዚህ ህፃናት የሚሰጡት ድጋፍ ምን እንደሚመስል ለማሳወቅ ይረዳል ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)  የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስስ አዲል ኮድር በቂ የማህበራዊ መስተጋብር ባለሙያዎች እንዲኖሩ ለማድረግ ከሚኒስቴሩ ጋር በመሆን የተቻላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ በበኩላቸው የማህበራዊ መስተጋብር ባለሙያዎችና አማካሪዎች በተቻለ መጠን እንድሟሉ እንሰራለን ብለዋል።

በስደት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች የምክር አገልግሎትና ጥቆማ የሚያደርሱበት የስልክ መስመር ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም