የወረርሽኙን ቀውስ ለመከላከል የተሰጡ መንግስታዊና ህብረተሰባዊ ምላሽ የተሰናሰሉ ናቸው --ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

91

አዲስ  አበባ  ሚያዚያ 20/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ቀውስ ለመከላከል የተሰጡ መንግስታዊና ህብረተሰባዊ ምላሾች ተሰናስለው መቀጠላቸውን የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

''ጥረቱ ግን ከመጣነው በላይ ሩቅ መንገድ መራመድ የሚያስገድድ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል'' ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ "ፈጠራ በቀውስ ጊዜ" በሚል መሪ ሃሳብ የቪዲዮ ውይይት ወይም ዌቢነር እየተካሄደ ነው።

ውይይቱን ከሚመሩት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች መካከል አንዷ የሆኑት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተደረጉና እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አብራርተዋል።

''ወረርሽኙ ማህበራዊ መስተጋብርን ያቃወሰ፣ መተሳሰብና መረዳዳትን የተገዳደረ፣ አብሮነትን የፈተነ፣ የደለቡ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የሚጋፋ ክስተት ቢሆንም ወረርሽኙን መዛመት የሚያስከትለውን ቀውስ ለመከላከል መንግሰታዊና ህብረተሰባዊ ምላሾች እየተሰጡ ነው'' ብለዋል።

በመንግስት ደረጃ  በወረርሽኙ ተጎጂ የሆኑ ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፎችን የፖሊሲ እርምጃዎች፣ የምግብ ዋስትና ችግሮችን ለመቅረፍ በግብዓት አቅርቦት፣ ተጋላጭ ለሆኖ ዜጎች ለመድረስ ሃብት በማሰባሰብ ስራዎች ረገድ በወረርሽኙ የሚደርሱ ጠባሳዎችን ለማሻር ይበል የሚሰኝ ስራ እየተከወናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በምግብ ባንክ ረገድም የአዲስ አበባን ተሞክሮ ወደክልሎች በማስፋት ከገጠር እስከ ከተማ የምግብ ባንኮች ለማቋቋም እየሰተራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሃይማኖት ቦታዎች የችግር ጊዜ መሸሸጊያ ቢሆኑም ጊዜው ለዚህ ባለመፍቀዱ ምዕመኑ በሰከነ መንገድ ከቤቱ እንዲከታተል በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት መደረጉንና በዚህም አወንታዊ ውጤቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በዲፕሎማሲ ረገድም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት ሚናዋ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ አገሮች ጋር በበሽታው መከላከል ጉዳዮች ያደረጓቸው የስልክ ውይይቶችም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ሚና ያመላከተ ወቅት መሆኑን አንስተዋል።

ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም እያደረገ ያለው ጥረት የተሰናሰለና መንግስትና ህዝብ ተደማምጠው እየተራመዱ መሆኑን ያሳየ እንደሆነ አመላክተዋል።

መንግስት ሀብት ማሰባሰብ ጥረቱ ከአንድ ብር ጀምሮ የአብሮነትንና ባለቤትነት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን፣ ወጣቶች ለራሳቸው ደህንነት ሳይሳሱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትርጉም ያለው ስራ ማከናወናቸውን አንስተዋል።

የኪነ ጥበብ ባለሙያቸው በሙያቸው እየተጉ መሆኑን፣ የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሳይሳሱ ለጋራ ዕጣ ፈንታ ሲሉ ወረረሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ ስራዎችን ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች በሽታውን ለመከላከል የሚያግዙ ምርቶች ላይ ማተኮራቸው፣ ባለሃብቶች ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ ማድረግና ቤትና ንብረታቸውን ለበሽታው መከላከል ጥረት መለገሳቸውን አስታውሰዋል።

የምግብ ዋስትና ችግርን ለመቅረፍ በጓሮ አትክልት ማምረት፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ስራዎች ላይ የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ በጋራ የተቃጣን ችግር በጋራ የመከላከል ነባር ልምዶችን ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በፌዴራልና በክልል ደረጃ የተቋቋሙ ግብረ ሃይላትም ተመጋጋቢ በሆነ መንገድ እየሰሩ መሆኑን ግልጸዋል።

በአጠቃላይ ኮቪድ 19ን ለመከላከል የሚተሰጠው መንግስታዊና ህብረተሰባዊ ምላሽ በተሰናሰለ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ያም ሆኖ ግን "ችግሩን ለመከላከል ከመጣነው በላይ የምንሄድበት ሩቅ መንገድ ይጠብቀናል" ያሉት ሚኒስትሯ፤ በመዘናጋት ዋጋ የከፈሉ አገሮች እጣ ፈንታ እንዳይደርስ የእስካሁን ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቀርበዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተወከሉት ዶክተር ታምራት ሃይሉ ኢትዮጵያ በክፉ ቀን ወቅቶች ታሪኳ አዳዲስ ፈጠራዎችና የመረዳዳት ባህሎች የጎለበቱበት ወቅት እንደነበር አንስተዋል።

ለአብትም በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በተከሰተው ቸነፈር በደረሰው የሰውና የእንስሳት እልቂት ከፍተኛ ርሀብ በመከሰቱ የምግብ ቀውስን ለመከላከል አዳዲስ የምግብ ባህል እርምጃዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

በወቅቱ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በርሀብ ለተጎዱ ወገኖች የቤት ለቤት ምግብ ማቅረብ የመረዳዳት ተግባራት መታየታቸውን፤ በገጠርም የእህል ጎተራቸውን ለአካባቢው ነዋሪ ያከፋፈሉ ባለጸጎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ከዚህ ቀደም ብሎ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የተከሰተውን ርሃብ ተከትሎ በቤተ መንግስት አካባቢ በርካታ ህዝብ በመሰብሰቡ ንፍሮ ከመቀቀል ባለፈ በቤተ መንግስት ያልተለመደ እንጀራን ፈርፍሮ ለዜጎች የማካፈል ተግባር መጀመሩን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ባለፈም 'ጥቁር ሞት'ን ጨምሮ በምዕራቡ ዓለም በተከሰቱ የክፉ ጊዜያት አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችና የምግብ ቀውስን ለመከላከል የሚያስችል አሰራሮች መፈጠራቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ወቅትም በታሪክ እንደተቀመጡ የችግር ጊዜ መፍቻ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችንና የአኗነር ባህሎች ገቢራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም