ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን አጠናቀው ለምረቃ መዘጋጀት አለባቸው--አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

74

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2012(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድሕረ ምረቃና የማታ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ አጠናቀው ለምረቃ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተገለፀ።

አስተያየታቸውን የሰጡ የዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በበኩላቸው የመመረቂያ ቀኑ መወሰኑ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸው እንዲራዘምላቸው ጠይቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቀጣዩ ሐምሌ ወር ላይ ጽሑፎቻቸውን ያጠናቀቁ የቀን ድህረ ምረቃና ሁሉንም የማታ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ አስታውቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንደሮው ዓመት በማታ እና በቀን የድሕረ ምረቃ የትምህርት መርሀግብሮች የሚመረቁ ተማሪዎች ከአማካሪዎቻቸው ጋር በመነጋገር ዝግጅት ማድረግ ይገባቸዋል።

ተማሪዎቹ ለምረቃ ጽሑፎቻቸው የሚያስፈልጋቸውን መረጃ የሚሰበስቡበትን መንገድ በመለወጥ ስልክና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በእዚህም ጠንክረው በመስራት ለምረቃ የሚያበቋቸውን ተግባራት ከወዲሁ መከወን እንዳለባቸው ነው ያስረዱት።

በተለይም ለምረቃ ጽሑፎቻቸው ቤተ-ሙከራ መግባት የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ቤተሙከራዎች ጽዱ ተደርገው በመዘጋጀቱ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲጠቀሙ መመቻቸቱን ተናግረዋል።

ነገር ግን ጽሑፎቻቸውን ማጠናቀቅ የማይችሉ ተማሪዎች ከአማካሪዎቻቸውና ከየትምህርት ክፍሎቹ ጋር በመነጋገር የጥናት ሥራቸውን መቀጠል የሚገባቸው መሆኑን አንስተዋል።

ዩንቨርሲቲው የመመረቂያ ስራቸውን በወቅቱ ማጠናቀቅ ያልቻሉትን  በመጪው ዓመት ጥቅምትና ሕዳር ወር ላይ ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ እንደሚያስመርቃቸውም አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተከታታይና ርቀት ትምህርት ቢሮ ዳይሬክተር ዶክተር ሙላቱ አስናቀ በማታና በርቀት ለሚማሩ የቅድመ-ምረቃና የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የፌስ ቡክ ገጽ ትላንት መልዕክት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው።

በዚህም ተማሪዎች በየትምህርት ክፍሎቹ ከተመደቡላችሁ አስተማሪዎች እና አማካሪዎች ጋር ለመገናኘት አማራጭ የመገናኛ መንገዶችን መጠቀም እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በእነዚህ መንገዶች ተጠቅመው ትምህርታቸውን መከታተልና የመመረቂያ ጽሁፎቻቸውን መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በበኩላቸው የመመረቂያ ጽሑፋቸውን ለማዘጋጀት በቤተ ሙከራ ተገኝተው መረጃዎችን ለመሰብሰብ ባለመቻላቸው ተቋሙ የመመረቂያ ቀኑን መወሰኑ አግባብ እንዳልሆነ ነው ለኢዜአ የገለጹት።

የማሕበራዊ ሳይንስ የትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችም ለመመረቂያ ጽሁፍ መሰብሰብ ያለባቸውን መረጃ አሟልተው ባለመጨረሳቸው "የምረቃ ቀኑ ሊራዘምልን ይገባል" ሲሉ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጪው ሐምሔ ወር ላይ ሁሉም የማታና የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ ከቀናት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም