'የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት ተጠናክሯል''... አምባሳደር ተሾመ ቶጋ

154

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2012( ኢዜአ) የኢትዮጵያና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከሩን  አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ።

የአፍሪካና ቻይና ግንኙነት መጎልበቱንም ተናግረዋል።


አምባሳደር ተሾመ ከቻይናው ''ግሎባል ታይምስ'' ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት በአገሮቹ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በሁለትዮሽ ጥቅምና በመከባበር ላይ የተመሰረተው ግንኙነት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላም አልተቀዛቀዘም ነው ያሉት።

ዘንድሮ አገሮቹ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 50ኛ ዓመት ወይም የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል የሚከበርበት እንደሆነ  አስታውሰው፣ባለፉት ዓመታት አገሮቹ በሁሉም ዘርፎች ግንኙነታቸውን ማጠናከራቸውን አመልክተዋል። 

"ይህ ግንኙነታችን በዚህ ፈታኝ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቴ ነው" ያሉት አምባሳደር ተሾመ፣አገሮቹ ወረርሸኙን ለመግታትና ቀጣይ ጉዞን ለማሳመር ዓለም በአቀፋዊ ስትራቴጂና ኅብረት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ልማት እገዛ እያደረገ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ተሾመ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ እክል ቢፈጥሩም፤ ሥራው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ኢኒሼቲቩ የአዲስ አበባ- ጅቡቲ የባቡር መሥመርን ፣የኢኮኖሚ ኮሪደሮችንና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ እንደሚያጠቃለል አመልክተዋል።


"በርካታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ሌሎች ፕሮጀክቶች አተገባበር ቢቀዛቀዝም፤ ሁኔታው መሻሻል ባሳየበት ቅፅበት ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምናለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለድንገተኛ ክስተት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ግብረ ኃይል ማቋቋሙንም ተናግረዋል።


አገሪቱ ወረርሽኙን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት"የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦትን ለማሟላት የውጭ አገራትንና የበጎ አድራጊዎችን ድጋፍ ትፈልጋለች" ብለዋል።

የኢትዮጵያና የቻይና የበሽታ መቆጣጠርና መከላከያ ማዕከላት በጋራ የአፍሪካ ኅብረተሰብ ጤና መሰረተ ልማትን እውን ለማድረግ በመረጃ ልውወጥ፣በባለሙያዎች አቅርቦት  አስፈላጊውን ሐብት በመመደብ  በመሥራት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።


ቻይና የኮቪድ 19 ወረርሽን ለመግታት የሚረዱ 12 የሕከምና ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመላኳ አምባሳደር ተሾመ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አፍሪካና ቻይና በጋራ ወረርሸኙን ለመግታት በመሥራት ላይ እንደሆኑ ያመለከቱት አምባሳደር ተሾመ፣"ወረርሽኙ በቀጣይ የአፍሪካ ቻይና ወዳጅነትን፣ትብብርንና ፣ህብረትን ያጠናክረዋል"ብለዋል።

የአፍሪካና የቻይና ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣የመከላከያ፣ማህበራዊና ባህላዊ ግንኙነት መጠናከሩንና  በተለይ የቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረምና የቤል ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ እውን ከሆነ በኋላ ትብብሩ እመርታ ማሳየቱን ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም