"ፈጠራ በቀውስ ጊዜ" የአዲስ ወግ ዌቢነር ውይይት በቪዲዮ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ይገኛል

80

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 20/2012 (ኢዜአ) "ፈጠራ በቀውስ ጊዜ" የአዲስ ወግ ዌቢነር ውይይት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

ውይይቱ ላይ በቀውስ ጊዜ የሚፈጠሩ አዳዲስ ችግሮችን ማለፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

ችግር ለፈጠራ መንስሄ በመሆኑ ችግር ፈቺ ፈጠራዎች ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ የቪዲዮ ኮንፈረንሱ አወያይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናግረዋል።

ሁሉም ስብሰባዎች በቪዲዮ ኮንፈርንስ እንዲደረጉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ውይይቶች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት እየተካሄዱና በቀጣይ የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንድትሸጋገር የሚያግዙ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ እንዲጸድቅ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኢ-ኮሜርስ፣ ኢ-ሰርቪስ፣ የኢ-ትራንዛክሽን አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለህዝብ ተወካዮች መላኩንም ተናግረዋል።

እነዚህን አገልግሎቶች በፍጥነት ስራ ላይ ለማዋል እየተሰራ ሲሆን ከ30 በላይ በቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ያላቸውን የቴክኖሎጂናአማራጭ እንዲያቀርቡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግስት ተቋማትን አገልግሎት ሰዎች በያሉበት ሆነው ለማግኘት እንዲችሉ "የኢ-ሰርቪስ" አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል የፈጠራ ስራ እየሰሩ ያሉ ሰዎች ለሚኒስቴሩ እንዲያቀርቡ እና እውቅና እንዲያገኙ ሁኔታዎች መመቻቸቱንም ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የኮሮናቫይረስ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ አስመልክተው የመወያየ ሃሳብ አቅርቧል።

ኮሮናቫይረስ በሰው ህይወትና በኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳትና በሽታውን ለመከላከል እየተደረገ ያልውን ጥረት አንስተዋል።

በፈጠራ ስራዎች ላይ በማተኮር ስራን በቀላሉ ለመስራት በሚቻልባቸው እና በቤት ውስጥ ሆኖ መስራትን የተመለከተም ሀሳብ አቅርበዋል።

ወይዘሮ ሙፈሪያት በዚሁ ወቅት አገሮች በሽታውን ለመከላከል አሁን ከሚሰሩት የበለጠ በቅንጅት መስራት እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ ሌላ የመወያያ ሃሳብ ያቀረቡት ዶክተር ታምራት ሃይሌ በዓለም ላይ በተለያየ ጊዜ የተከሰቱና ጉዳት ያደረሱተን በሽታዎችን በተመለከተ ሃሳብ አቅርበዋል።

በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ባለፉት ሁለት ክፍለ ዘመናት በተከሰቱት ወርርሽኝ ህይወታቸው ማለፉን አንስተው፤ በዚሁ ጊዜ አገሮች በሽታውን ለመቋቋም የተለያዩ ርምጃዎች መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ባህላዊና ዘመናዊ ህክምናቸውን ከመስጠት በተጨማሪ ሰዎችን በአንድ ቦታ የማቆት ስራ መለመዱን ጠቁመዋል።

''የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች እንዲለመዱ ተደርጓል'' ብለዋል።

አቶ ዩሱፍ ራጃ በበኩላቸው ኮሮናቫይረስ በዓለም ላይ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በተለይ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ገልጸው፤ ይህም ሰዎች ሌላ አማራጭ እንዲጠቀሙ ማድረጉን ገልጸዋል።

''በዚህም ሰዎች በኢንተርኔት አማካይነት ስራ እንዲሰሩ፣ ምርቶችን በኦንላይን በማዘዝ ለፈላጊዎች የማቅረብ ስራ እንዲሰራ አድርጓል'' ብለዋል።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ በርካታ ሰዎች ቤት ሆነው እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

''በኢትዮጵያም በኢንተርኔት የመገበያየት እና የስራ እድል እየተፈጠር ይገኛል፤ ስብሰባዎች በኢንተርኔት እየተካሄዱ ይገኛል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም