በታዋቂ አትሌቶች መሪነት በኢንተርኔት የታገዘና በቀጥታ ቪዲዮ የሚሳተፉበት የቨርቿል ሩጫ እየተዘጋጀ ነው

89

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2012(ኢዜአ) በታዋቂ አትሌቶች መሪነት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሳትፍ በኢንተርኔት የታገዘና በቀጥታ ቪዲዮ የሚሳተፉበት የቨርቿል ሩጫ እየተዘጋጀ ነው።

ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የታላቁ አፍሪካ ሩጫ አዘጋጅ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በብርቅዬ አትሌቶች መሪነት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሳትፍ የቨርቿል ሩጫ አየተዘጋጀ ስለ መሆኑ አስታውቋል።

በዝግጅቱ ላይ ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኔሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ስለሺ ስህን፣ ፋጡማ ሮባ፣ ሚሊዮን ወልዴ እና እጅጋየሁ ዲባባ እንደሚገኙበት ተገልጿል።

የውድድሩ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ እንደገለፁት፤ የኮቪድ 19 በሽታ በዓለም ዙሪያ ከፈጠረው የጤና ፈተና ጎን ለጎን፣ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እያደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ደግሞ ወረርሽኙ በበረታባት አሜሪካና አውሮፓ የሚገኙ ኢትዮያዊያን ከተለመደው የአኗኗር ዘይቤ በወጣ ፣ ረዘም ላለ ጊዜ ቤት ውስጥ ለመቀመጥ በመገደዳቸው፣ ሥራ አንደ ወትሮው ወጥቶና ነፃ ሆኖ መስራት አለመቻላቸውን ገልፀዋል።

ይሄ ደግሞ በበርካቶች ላይ ስጋትና የአዕምሮ ጭንቀት በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ዶክተር ጋሻው ይሄንን ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ ለመቀየር የሚያግዝ በኢንተርኔት በቤትና ግቢ ውስጥ ሆነው የሚሮጡት የቨርቿል ሩጫ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

አንጋፋና ብርቅዬ አትሌቶች የበኩላቸውን ለማበርከት በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሳትፍ፣ የኢትዮጵያ ቨርቿል በታላቁ ሩጫ በዲሲ አስተባባሪነት ቅዳሜ፣ ግንቦት 8 ላይ እንደሚካሄድ ነው የገለፁት።

ዝግጅቱ አትሌቶች በየአሉበት ቦታ ሆነው፣ በቪዲዮ ተራ በተራ እየሮጡ ለውድድሩ በተዘጋጀ ዙም (Zoom) በተሰኘ መተግበሪያ ላይ በቀጥታ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሳታፊዎች ጋር የሚሮጡበት ነው ብለዋል።

በፌስቡክ ላይቭ እና ዩቲዩብ ላይቭ ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍል ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በተመሳሳይ ሰዓት በአንድ ላይ የሚያሳትፍ፣ ሁሉን ኢትዮጵያዊ የሚያሰባስብ የሩጫ ወይም የሶምሶማ ዝግጅት መሆኑ ተገልጿል።

ተሳታፊዎችም በቤት ውስጥ ወይም ግቢ ውስጥ፣ የመሮጫ ማሽን ያላቸው ደግሞ ማሽኑ ላይ ሆነዉ እየሮጡ በስልካቸው፣ በኮሚፒውተር ወይም ከቴሌቪዠን ጋር አገናኝተዉ አትሌቶችን እየተከተሉ የሚሳተፉበት ዝግጅት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዙም (Zoom) መተግበሪያ ላይ በቀጥታ የሚሳተፉት ሰዎች ከሌሎች በየትኛውም የዓለም ክፍል ከሚኖር ኢትዮጵያዊያን ጋር እየተያዩና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው የሚካፈሉበት ውድድር ሲሆን፣ ይህ እድልም ቀድመው ለሚመዘገቡ 1 ሺህ የቴክኖሎጂው አቅም ለሚፈቅደው ሰዎች የሚቀርብ ይሆናል።

ከዝግጅቱ የሚገኘው ገቢ በኮቪድ 19 ዙሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሰሩ ሁለት መንግስታዊ ያልሆኑና በኢትዮጵያዊያን የሚመሩ አነስተኛ ድርጅቶች የሚበረከት እንደሆነ ነው የገለፁት።

ቨርቿል ሩጫ /Virtual Race/ የሚባለው ከየትኛውም ቦታ እና አካባቢ በመሆን የሚከናወን ሩጫ ወይንም ፈጠን ያለ የእርምጃ ውድድር እንደማለት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም