በኮሮና ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች 3 ሚለዮንን ተሻገረ

54

አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 19/2012 (ኢዜአ)በአለም ላይ በኮሮና ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን በላይ አለፈ ።

የአገሮች በወረርሽኙ ምክንያት ጥለዋቸው የነበሩ ክልከላዎችን እያነሱ መሆናቸውም ተገልጿል።

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ በኮሮና ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት በመጨመር ከ3 ሚሊዮን በላይ ሆኗል።

በወረርሽኙ ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

በበሽታው ከተያዙት ውስጥ ወደ 900 ሺህ የሚጠጉት ማገገማቸውም ተገልጿል።

የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል አገሮች ጥለውት የነበረውን ክልከላ ቀስ በቀስ እያነሱ መሆኑን የቻይና ዜና አገልግሎት በዘገባው አመልክቷል።

በዚህም አገሮች በቤት ውስጥ መቆየትን የሚያካትተው ገደብ በማንሳት ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታቸው እንዲያገግም ማድረግ ጀምረዋል።

ከነዚህ መካከል ከ22 ሺህ በላይ ዜጎቿን በወረርሽኙ ያጣችው ፈረንሳይ ተጠቃሽ ናት።

የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤድዋርድ ፊሊፒ ተጥለው የነበሩ ክልከላዎች መነሳትን አስመልክቶ የመንግስታችውን እቅድ ነገ ለፓርላማ እንደሚያቀርቡ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

በአገሪቱ በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ ለጤና ተቋማት እፎይታን ሰጥቷል።

በመሆኑም ከግንቦት 3 ጀምሮ ክልከላዎችን ለማንሳት ማቀዷን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በወረርሽኙ የተያዙባት ሰዎች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን እየተጠጋ የሚገኘውና ከዓለም ቀዳሚ የሆነችው የአሜሪካ ክልሎች ክልከላዎችን ማንሳት ጀምረዋል።

የአገሪቱ የመንግስት ኃላፊዎች እንዳስታወቁት የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴን ለማስጀመር በቀጣዮቹ ሳምንታት የኮቪድ-19 የመመርመር አቅምን እጥፍ እናደርጋለን ብለዋል።

ኦስትሪያ፣ ዴንማርክና ኖርዌይ የተወሰኑ ክልከላዎችን ካነሱ የአውሮፓ አገሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ኮሮና ባለፉት አራት ወራት ዓለምን ባዳረሰ መልኩ ተከስቶ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይታወቃል።

አንዳንዶችም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተከሰተ ''ጦርነት'' ብለውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም