በኮሮናቫይረስ የተያዘን ሰው ለመተንፈስ የሚያግዝ የፈጠራ ውጤት ተገኘ

60

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2012(ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ የተያዘን ሰው በድንገተኛ ክፍል ለመተንፈስ የሚያግዝ የመተንፈሻ መሳሪያ በኢትዮጵያዊያን የፈጠራ ባለሙያ ወጣቶች ተሰራ።

በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ከሚያሳያቸው ምልክቶች አንዱ ለመተንፈስ መቸገር ነው።

የቫይረሱ ህመም እየባሰ ሲሄድ የመተንፈሻ አካላትን ስለሚያዳክም ሕመምተኛው የመተንፈሻ መሳሪያ ወይም የቬንትሌተር እገዛ ካልተደረገለት ለመተንፈስ ይቸገራል።

በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ መስፋፋቱን ተከትሎ መሳሪያውን ለማግኘት እጥረት መኖሩ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህን ችግር የተረዱት ኢንጂነር ማዕሩ ኡመር እና ቀረመንዝ ካሳዬ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው የጽኑ ሕሙማን ክፍል እስኪገባ ድረስ ለመተንፈስ የሚያግዝ "ኢመርጀንሲ መካኒካል ቬንትሌተር" መሳሪያ ፈጥረዋል።

የኤሌክትሮመካኒካል ኢንጂነር የሆነው ወጣት ማዕሩ ኡመር በዓለም እንዲሁም በኢትዮጵያ ያለውን የቬንትሌተር እጥረት በመረዳት እውቀታቸውን ተጠቅመው መሳሪያውን እንደፈጠሩት ነው የገለጸው።

እንደወጣቱ ገለጻ መሳሪያው ሕመምተኛው ለመተንፈስ በሚቸገርበት ወቅት እገዛ የሚያደርግለትን ዋና ቬንትሌተር እስኪያገኙ ድረስ በድንገተኛ ክፍል ውስጥ ለመተንፈስ የሚያስችለው ነው።

ይህም በአሁኑ ወቅት ነርሶች በእጅ እየሰጡት ያለውን የሕክምና እርዳታ የሚተካ የፈጠራ ውጤት መሆኑን ነው ባለሙያው የተናገረው።

ይህ የፈጠራ ውጤት በድንገተኛ ክፍል በሰው ኃይል ይደረግ የነበረውን እገዛ በማስቀረት በራሱ የህክምና ድጋፍ መስጠት የሚያስችል መሆኑንም አመልክቷል።

የፈጠራ ውጤቱ ህመምተኛው የሚተነፍስበትን ደረጃም መቆጣጠር በሚያስችል መልኩ እንደተሰራም የፈጠራ ባለሙያው ያብራል።

አሁን ባለው ደረጃም መሳሪያው በድንገተኛ ሕክምና የመተንፈስ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ተናግሯል።

ከውጭ ተገዝቶ የሚገባ አንድ የመተንፈሻ መሳሪያ እስከ 20 ሺህ ዶላር የሚጠይቅ  ሲሆን ወጣቶቹ የፈጠሩትን መሳሪያ ግን እስከ 20 ሺህ ብር በሚደርስ ወጪ ሰርተው ማቅረብ እንደሚችሉ ነው ያስረዱት።

በመሆኑም የሚመለከተው አካል ትብብር ቢያደርግ መሳሪያውን ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚችል ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ የፈጠራ ስራውን ለማከናወን የተለያዩ አገር ኢንጂነሮች ያለውን የቬንትሌተር እጥረት ችግር ለመፍታት ሲሉ ያበረከቷቸውን ተመሳሳይ የፈጠራ ውጤቶች በሞዴልነት መጠቀማቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም