ትራንስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ አየር መንገድን ፈጣን የለውጥ ሂደት አደነቀ

186
አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2010 ትራንስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስከ 2025 (እ ኤ አ) የያዘውን እቅድ ለማሳካት ያለውን ፈጣን የለውጥ ሂደት አደነቀ። ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በየዓመቱ 4ሺህ ሰልጣኞችን የማስተናገድ አቅም ያለውን የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ወይም ምስለ በረራ፣ የበረራ አስተናጋጆች ማሰልጠኛ የአቪየሽን አካዳሚ የጥገና እና ሌሎች ክፍሎችንም ጎብኝተዋል። አየር መንገዱ የነደፈውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያከናውነውን የለውጥ ተግባር አፈፃፀም የሚደነቅ እንደሆነ በጉብኝታቸው ወቅት ተናግረዋል። 'እያንዳንዱን የአየር መንገዱን ክፍሎች በጥልቀት በዚህ ደረጃ ስመለከት የመጀመሪያዬ ነው' ያሉት ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ተቋሙ ከሚገመተው በላይ መለወጥ እንደሚቻል ለዓለም ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል። አብዛኛው የአገሪቱ ህዝብ በሪፖርት ከሚሰማው በላይ የአየር መንገዱ ክፍሎች እጅግ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የተራጁና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ መሆን የሚችል ትልቅ ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል። ከማሰልጠኛ ተቋማት ጀምሮ ምናልባትም ብዙ አየር መንገዶች የሌሏቸውና የሌሎች አገር ዜጎችም የሚገለገሉበት ከተሰራ በሌሎች ዘርፎችም ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል። ተቋሙ 'እ ኤ አ በ2025 እደርስበታለሁ' ብሎ የያዘውን ራዕይ ለማሳካት ተግበሩን አጠናክሮ ከቀጠለ እቅዱን ቀድሞ ማሳካት ያስችለዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። የትራንስፖርት ሚኒስቴር አየር መንገዱ በተናጠል ሊወጣቸው የማይችሉ ችግሮች ሲያጋጥሙት በጋራ ለመፍታት መዘጋጀቱንም ጨምረው ገልፀዋል። የኢትዮዽያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በበኩላቸው አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለመጨመርና ሰፋፊ የበረራ ጣቢያዎቸን ለመክፈት የሚሰሩ ስራዎች የአጋር አካላትን ድጋፍ የሚፈልጉ በመሆናቸው  ከሚኒስቴሩ ጋር ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት 113 አለም ዓቀፍ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮዽያ አየር መንገድ ከሌሎች አየር መንገዶች ድርሻ በመግዛት ይዞታዎቹን የበለጠ ለማስፋትና አገራዊ ዲፕሎማሲን ጭምር ለማሳደግ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር በተጨማሪ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር አብሮ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። እንደ ሞዛምቢክ፣ ዛምቢያ፣ ጊኒ፣ ቻድ፣ ጅቡቲ በመሳሰሉት አገሮች አየር መንገዱ የማስፋፊያ እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ተነግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም