የዲላ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዙ የፈጠራ ውጤቶችን እያመረተ ነው

67

ዲላ፤ ሚያዝያ 17/ 2012 (ኢዜአ) የዲላ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዙ የፈጠራ ውጤቶችን በማምረት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገለፀ ።

የኮሌጁ ዲን አቶ ግርማ ዶሪ ለኢዜአ እንደገለፁት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያግዙ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን ለህዝብ በማድረስ  ኮሌጁ የበኩሉን እየተወጣ ነው።

ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነ የእጅ መታጠቢያና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አምርቶ ለህብረተሰቡ ማስራጨቱንም ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ማስክ መጠቀም ግዴታ የሚሆን ከሆነ የአቅርቦት ችግር እንዳይከሰት ኮሌጁ እያመረተ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ በጌዴኦ ዞን የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ማስክ ማምረት እንዲችሉ ኮሌጁ  የእውቀት ሽግግር እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የተመረቱ የእጅ መታጠቢያዎች ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ከማስቀመጥ ባለፈ ህብረተሰቡ እራሱን ከቫይረሱ እንዲጠብቅ የማስተማር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በማቆያ ማዕከላት የአልጋ እጥረት እንዳይከሰት አምርቶ እያቀረበ መሆኑን የጠቆሙት  አቶ ግርማ፤ አልጋውን በብዛት ለማምረት የሃብት ውስንንት በመኖሩ ከተቋማትና ከግል ድርጅቶች ጋር በቅርበት ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሌጁ በቀን ከ400 በላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች እያመረተ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ በኮሌጁ የጋርመንት ዲፖርትመንት መምህር ቴድሮስ ሽብሩ ናቸው።

የሚመረተው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ታጥቦ ዳግም አገልግሎት ላይ መዋል የሚችል መሆኑን የጠቆሙት መምህር ቴድሮስ፤ በቀጣይ ኮሌጁ የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ኢንተርፕራይዞች በማሸጋገር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችሉ የግብዓቶች እጥረት እንዳይከሰት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ የኮሮና መከላከያ ግብረ ሀይል ሰብሳቢ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው በዞኑ የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ኮሌጁን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ተቋማት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እያደረጉት ያለው ጥረት አበረታች መሆኑንም ገልጸዋል።

የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ አንጻር በተለይም አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ረገድ የሚስተዋሉ መዘናጋቶችን ለመቅረፍ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም