በቤንች ማጂ ዞን የተከሰተው ተምች በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራው ውጤት አምጥቷል

58
ሚዛን ሰኔ 26/2010 በአካባቢው ሰብል ላይ ተከስቶ የነበረውን የአሜሪካ መጤ ተምች በባህላዊ መንገድ ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የቤንች ማጂ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ አስታወቀ፡፡ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ደስታ ግርማዬ ለኢዜአ እንዳሉት  በ3ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ የተምች ተባይ ተከስቷል፡፡ ተባዩን ለመከላከል ካለፈው ዓመት ልምድ በመወሰዱ ዘንድሮ ጉዳት ሳያደርስ በባህላዊ መንገድ ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡ ተምቹ ከተከሰተው የሰብል መሬት ውስጥ እስካሁን   ሦስት ሺህ ሄክታር የሚሆነውን በባህላዊ መንገድና ቀሪውን በኬሚካል መከላከላቸውን አስረድተዋል፡፡ ለአርሶ አደሩ ማሳውን ቶሎ ቶሎ እንዲጎበኝና በባህላዊ ዘዴ ተባዩን እንዲያጠፋም በቂ ግንዛቤ መሰጠቱን ወይዘሮ ደስታ ተናግረዋል፡፡ "ተባዩ በመደበኛነት ቀጣይነት ያለውና የተለያየ የሰብል ዓይነቶችን ስለሚያጠቃ በየዓመቱ በቀላሉ መከላከል ስለሚቻልበትም ልምድ ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡ በደቡብ ቤንች ወረዳ የዘሚቃ ቀበሌ አርሶ አደር አቶ አበራ ቢረጋ በሰጡት አስተያየት በአንድ ሄክታር የበቆሎ ማሳቸው ላይ የተምች ተባይ ተከስቶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በየቀኑ ጧትና ማታ በመከታተልና ሲከሰትም በእጅ በመግደል በቀላሉ መቆጣጠር መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ተባዩ አዲስ ስለነበር ጥፋት እንዳደረሰባቸው  አስታውሰው "በዚህ ዓመት ኬሚካል ሳንጠብቅ በደቦ በባህላዊ መንገድ አጥፍተነዋል" ብለዋል፡፡ ከማሳቸው የተከሰተውን ተምች በእጅ በመልቀም  መከላከላቸውን የተናገሩት ደግሞ በሰሜን ቤንች ወረዳ የጋሪቅን ቀበሌ አርሶ አደር አቶ ጴጥሮስ ዘጋርያስ ናቸው፡፡ አርሶአደሩ እንዳሉት ባህላዊ የአወጋገድ ዜዴ ከኬሚካሉ የተሻለ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም