በአዲስ አበባ ለቀጣይ 3 ወራት የሚቆይ 'ትምህርት በቤቴ' የተሰኘ የቴሌቪዥን መርሃ ግብር መሰጠት ተጀመረ

112

አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2012 (ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ 19) ምክንያት መደበኛ ትምህረት መቋረጡን ተከትሎ ለቀጣይ ሶሰት ወራት የሚቆይ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር በአፍሪ ሔልዝ ቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል መጀመሩን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

መደበኛ ትምህርት እስኪጀመር ድረስ ተማሪዎች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ወላጆች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱና የአፍሪ ሄልዝ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሜሎን በቀለ መርሃ ግብሩን አስመልክቶ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስጋት የተነሳ ላለፉት 45 ቀናት መደበኛ ትምህርት መስተጓጎሉን ተከትሎ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተነጥለው በቤት ውስጥ በመሆናቸው ከ1ኛ እስከ 7 ክፍል ተማሪዎች በሬዲዮ ትምህርት እንዲከታተሉ አማራጭ መቀመጡን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተማሪዎች ዋና ዋና የትምህርት ይዘቶችን በአጭሩ በማዘጋጀት ማህበራዊ ሚዲያና በቢሮው ድረ-ገጽ በመጫን ተማሪዎች ከኢንተርኔት በማውረድ እንዲያነቡ አማራጭ ማቅረቡንም አቶ ዘላለም ገልጸዋል።

ከ7ኛ አስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ከሚያዝያ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣይ ሶሰት ወራት የሚቆይ "ትምህርት በቤቴ" የተሰኘ የትምህርት መርሐ ግብር በአፍሪ ሔልዝ ቴሌቪዥን ጣቢያ መጀመሩን ገልጸዋል።

የቢሮ ሃላፊው በቴሌቪዥን ትምህርት ከነዋሪዎች የኑሮ ደረጃ አኳያ በከተማዋ ተማሪዎች ዘንድ ምን ያህል ተደራሽ እንደሚሆን ሲገልፁም፤ ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢ በአዲስ አበባ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

መርሃ ግብሩ መደበኛ ትምህርትን ለመተካት ሳይሆን ተማሪዎች ቤት ሲውሉ ለሌሎች ማህበራዊ፣ ስነ ምግባራዊና ስነልቦናዊ ጫናዎች ሳይጋለጡ በትምህርት ድባብ ውስጥ እንዲቆዩና ወደ መደበኛ ትምህርት ገበታ ሲመሉም የመዘናጋት ስሜት እንዳይፈጠር በማለም እንደሆነ ገልጸዋል።

እንዲሁም በቀጣይ ለሚሰጡ አገራዊና ክልልዊ ፈተናዎች ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉም ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመሆኑም ወላጆች፣ መምህራንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተማሪዎች ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት እስኪመለሱ ድረስ በአፍሪ ሔልዝ ቴሌቭዥን በኩል ትምህርት እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

መደበኛ ትምህርት የተቋረጠው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ተማሪዎች ቤታቸው ይውላሉ በሚል እሳቤ መሆኑ አንስተው፤ ነገር ግን በየመንገዱ በመዝናኛ ስፍራዎች ላይ የሚታዩ ተማሪዎችን ወላጆች ሃላፊነት ወስደው ከተግባራቱ ተቆጥበው ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ከቴሌቪዥኑ ትምህርት መርሀ ግብሩ ተማሪዎች ወደ 8455 'E' ብለው በአጭር የጽሁፍ መልዕክት በጥያቄና መልስ ውድድር በመሳተፍ የተለያዩ ሽልማት እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ''ይህም በሳምንቱ የተማሩትን ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ገቢራዊ ይደረጋል'' ነው ያሉት።


መደበኛው ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ በፌዴራል መንግስት የሚወሰን መሆኑንም አመልክተዋል።

የአፍሪ ሔልዝ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሜሎን በቀለ ጣያው ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣትና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የበኩሉን ሚና ለመጫወት በቀጣይ 90 ቀናት የሙሉ ቀን ትምህርት መርሃ ግብር ለማስተላለፍ መወሰኑን ተናግረዋል።

በሳምንት 30 ክፍለ ጊዜዎች ያሉት የ'ትምህርት በቤቴ' መርሃ ግብር በገንዘብ ቢገመት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ገልጸዋል።

በትምህርት አሰጣጥም በተለይ የመምህራን ጣልቃ ገብነት የሚጠይቁ የሂሳብ፣ የስነ ሕይወት፣ የፊዚክስና የኬሚስትሪ እንዲሁም የታሪክና የጂኦግራፊ ትምህርት ዓይነቶችን ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች ከ30 በላይ በሆኑ መምህራ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የትምህርት አሰጣጥም በአዲስ አበባና አካባቢው በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ለሚሰጡ ትምህርት ቤቶች ሲባል በኦሮምኛ ቋንቋ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ስለመኖራቸውም ተናግረዋል።

የትምህርት መርሃ ግብሩ ለየት የሚያደርገው ቀለል ባለ፣ በሚያዝናና ተማሪዎችን  በማያሰለች አቀራርብ መሆኑ፣ ሽልማትና ማበረታቻ ዝግጅቶች መኖራቸው፣ ትልልቅ ሰዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትና አጫጭር ዶክመንተሪዎች የሚቀርቡበት መሆኑን ገልጸዋል።

በሳምንታዊ ጥያቄና መልስ ውድድር 8455 ላይ በመላክ የሚያሸንፉ ተማሪዎችና ከመምህራን ለሚሰጡ ጥያቄዎች መልስ የሚመልሱ ተማሪዎች ሽልማትና እውቅና እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ የሚቀርበውም ዘወትር ከሰኞ እስከ አርብ ጠዋት ከ3 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ከ30 እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከ8 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ከ30 መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም