በትግራይ ከ400ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሊሰማሩ ነው

70
መቀሌ ሰኔ 26/2010 በትግራይ ክልል በተያዘው የክረምት ወቅት ከ400ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሚሰማሩ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ አቶ ነጋ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚሰማሩ ወጣቶች 35ሺህ ያህሉ  የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ናቸው። የልማት ስራ ከሐምሌ2010ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ወራት የሚቆይ ሲሆን ከ35 ሚሊየን በላይ ችግኞች ይተከላሉ፤10ሺህ ለሚሆኑ  አረጋዊያንና የሰማዕታት ቤተሰብ አባላት የእርሻ መሬታቸውን በማረስ የመዝራትና የመኮትኮት ተግባራት ያከናውናሉ ተብሏል። በጤና ዘርፍም የደም ልገሳና በየአካባቢያቸው የሚገኙ ለወባ በሽታ የሚያጋልጡ ረግረጋማ ቦታዎች የማጽዳት ስራዎችም እንዲሁ። 10ሺህ ለሚሆኑ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ በስራው ለመሳተፍ ከተዘጋጁት  መካከል የአዲግራት ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ዛይድ ፀጋይ በሰጠችው አስተያየት " ህፃናትና አረጋዊያንን በጉልበት ለማገዝና  ከተማችንን ለማስዋብ ተዘጋጅተናል "ብላለች ። የመረብ ለኸ ወረዳ ወጣት ማህሌት ኪሮስ በበኩሏ የዛፍ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ አካባቢያቸውን በአረንጓዴ ልማት ለማስዋብ ከጓደኞቿ ጋር ስልጠና ወስዳ ለስራው መሰናዳቷን ተናግራለች፡፡ " ክልላችንን ብሎም ሀገራችንን ለማልማት የተሰጠንን ኃላፊነት በመወጣት በተግባር ሰርተን ሌሎች እንዲሰሩ ለማነሳሳት ተዘጋጅተናል" ያለው ደግሞ የአድዋ ከተማ ነዋሪው  ወጣት ተመስገን አብርሃ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት   ከ200 ሺህ በላይ ወጣቶች በተለያየ የልማት ዘርፍ ተሰማርተው የበጎ ፍቃድ መስጠታቸውም ተመልክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም