በቀጣዮቹ አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገፅታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለፀ

59
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2010 በቀጣዮቹ አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ገፅታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና በአንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የብሄራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለፀው ዝናብ ሰጪ የሜቲዎሮሎጂ ክስተቶች ሁሉንም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ ስፍራዎች የሚያዳርሱ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ነጎድጓዳማ እና በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ይዘወተራል። አብዛኞቹ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ጥሩ የእርጥበት ስርጭት እንደሚያገኙ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ለመኸር የግብርና ስራ እንቅስቃሴ የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው መግለጫው ያብራራው። የመኸር ሰብል አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የአፈር ውስጥ እርጥበትን የሚያሻሽል በመሆኑ የመኸር ሰብሎችን በወቅቱ ለመዝራት ምቹ እንደሆነ በመግለፅ የሚገኘው እርጥበት አስቀድመው ተዘርተው በተለያዩ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የረጅም ጊዜ ሰብሎች እድገት በጎ ጎን ይኖረዋልም ብሏል። በአንዳንድ ቦዎች ከፍተኛ የእርጥበት ሁኔታ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ለጎርፍ መከሰትና ለመሬት መንሸራተ ማጋለጡና ከመጠን በላይ ውሃ ማሳ ላይ እንዲተኛ ስለሚያደርግ አርሶ አደሩ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስቧል። ይህም በእርሻ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያደርስ ቦይ በማውጣትና የማንጣፈፍ ስራ በመስራት ሰብሉ በጎርፍ ታጥቦ እንዳይወሰድ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ነው ኤጀንሲው ያሳሰበው። በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚገኘው እርጥበት ለመጠጥ ውሃ እና ለግጦሽ ሳር ልምላሜ ጥሩ አስተዋፅኦ እንዳለውም ነው የተገለፀው። በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው ክረምት ተጠቃሚ ተፋሰሶች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ የተገለፀ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚኖርም ነው መግለጫው ያብራራው። በተጨማሪም የወንዞች ሙላት ሊፈጠር ይችላል ያለው ኤጀንሲው በዚህ ሳቢያ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት ቅድመ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም