የአዳማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በሴንሰር የሚሰራ የእጅ መታጠቢያ መሳሪያ ለአገልግሎት አበቃ

186

አዳማ ሚያዝያ 15/2012 (ኢዜአ) የአዳማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በሴንሰር የሚሰራ የእጅ መታጠቢያ ቴክኖሎጂን በምርምር በማውጣት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገለጸ። 

የኮሮና በሽታን ለመከላከል ከሚረዱት አንዱ እጅን አዘውትሮ መታጠብ ነው።

ስጋቱን ለመቀነስ ደግሞ ተቋማትና ግለሰቦች ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆኑ የእጅ መታጠቢያ ማሽኖችን እየሰሩ ነው።

የአዳማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነና በሴንሰር የሚሰራ የእጅ መታጠቢያ ሰርቶ ይፋ አድርጓል።

አጠቃቀሙ ቀላልና ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ መሆን እንደሚችል የሚገልፀው የፈጠራው ባለቤትና በኮሌጁ የኤሌክትሮ ቴክኖሎጂ ተማሪ ሙሉቀን ታምሩ ነው ።

ቴክኖሎጂውን በአካባቢው ከሚገኙት ቁሳቁሶች በመስራት ለህዝብ አገልግሎት እንዲበቃ ማድረጉን የገለጸው ተማሪው የኮሮና በሽታን ለመከላከል ከምናውለው አገልግሎት ባለፈ በቀጣይነት ለድርጅቶችና ለግለሰቦች ጭምር ተደራሽ እንዲሆን እየሰራን ነው ብሏል።

የኮሌጁ ዲን አቶ ተሻለ ዱጉማ በበኩላቸው ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የመታጠቢያ ቴክኖሎጂን በምርምር በማውጣት ኮሌጁ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የአፍና ፊት መሸፈኛ ጭምብል አምርተው ለህብረተሰቡ ማቅረባቸውን የሚናገሩት ዲኑ ማህበረሰቡ ከ1 ሺህ ብር በታች በሆነ ወጪ ቴክኖሎጂውን በመግዛት በቤቱ ጭምር ሊጠቀምበት እንደሚችልም አስረድተዋል።

የአዳማ ፖሊ ቴኪኒክ ኮሌጅ በተጨማሪም በከተማዋ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ዱቄትና ሌሎች ድጋፎች ማድረጉን ከኮሌጁ ዲን ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም