ልደታ ክፍለ ከተማ ለአቅመ ደካማ ሙስሊም የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

100

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2012(ኢዜአ) በአዲስ አበባ  ልደታ ክፍለ ከተማ በነገው እለት የሚገባውን የረመዳን ፆም ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ ሙስሊም የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብና የገንዝብ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ የተሰባሰበው ከአካባቢው ባለሀብቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብና ነዋሪዎች ሲሆን፤ ለህብረተሰብ ክፍሎቹ ከገንዘብ በተጨማሪ ዱቄት፣ ዘይት፣ ሩዝና ቴምር ተበርክቷል።

የእስልምና ሃይማኖት መምህር ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት የኮሮናቫይረስን መቋቋም የሚቻለው እንደ ማህበረሰብ በተባበረ ክንድ መንቀሳቀስ ሲቻል ነው።

ክፍለ ከተማውም ይህን በመረዳት ህዝቡን በማስተባበር ያደረገው ድጋፍ እንደሚያስመሰግ ተናግረዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መሪዎች ወደ ህዝቡ ወርደው እየሰሩት ያለው በጎ ስራም የሚበረታታ መሆኑን ኡስታዝ አቡበከር ተናግረዋል።

"መሪዎች እየሰሩት ያለው ሥራ በቀጣይም የበለጠ እንዲጠናከር ህዝቡ ከጎናቸው በመቆም ሊያበረታታቸው ይገባል" ብለዋል።

እንደእዚህ ባለው ድጋፍ እድሮችም ጭምር ሊሳተፉ እንደሚገባና ሰው በህይወት እያለ መረዳዳትን ባህል እያደረጉ መምጣት የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ምህረት በበኩላቸው በቅርቡ የተከበረውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ አቅም ለሌላቸው የክርስትና እምነት ተከታዮች  መሰል ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው፤ ድጋፉን በማድረግ በኩል ወጣቶች እየሰሩት ያለው ሥራ ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት።

ወጣቶቹና በክፍለ ከተማው የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ከፍሎች ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም የከፋ ጉዳት በደረሰ ጊዜ አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ኢሳያስ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም