በደብረ ብርሃን ከተማ ባለ ሦስት እግር አሽከርካሪዎች ከተመን በላይ እያስከፈሉን ነው ሲሉ ነዋሪዎች ገለጹ

77
ደብረ ብርሃን ሰኔ 26/2010 በደብረ ብርሃን ከተማ የሚሰሩ ባለ ሦስት እግር አሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው የትራንስፖርት ታሪፍ በላይ ሒሰብ እያስከፈሉን ነው ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ። የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ከታሪፍ በላይ ሒሳብ በሚጠይቁ ህገ ወጥ ባጃጅ አሽከርካሪዎች ላይ የቅጣት እርምጃ መውሰድ እንደጀመረ ተናግሯል። በደብረ ብርሃን ከተማ የቀበሌ 09 ነዋሪ አቶ ሽዋወርቅ እሸቴ ለኢዜአ እንደገለፁት ባጃጅ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈል ለአላስፈላጊ ወጭ እየዳረጓቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከታክሲ ተራ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የመንግስት ታሪፉ 2 ብር ከ82 ሳንቲም ቢሆንም አሽከርካሪዎቹ በህገ ወጥ መንገድ ከ4 እስከ 5 ብር እንደሚያስከፍሏቸው ተናግረዋል፡፡ በሌሎች መስመሮችም ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ ከ50 ሣንቲም አስከ 3 ብር ጭማሬ እንደሚጠየቁ ተናግረው፣ ምክንያቱን ሲጠይቁ "ቤንዚል በመጥፋቱ ጨምረን ነው የምነገዛው ካልተመቸህ ውረድ" እንደሚባሉና በእዚህም ከስራቸው እየተጉላሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ለሥራ ጉዳይ በቀን ከሦስት ጊዜ በላይ በባጃጅ ስለሚንቀሳቀሱ ዘውትር ከአሽከርካሪዎች ጋር በመጨቃጨቅ መማረራቸውን ጠቁመው የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ በከተማው የቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ ምትኩ በላይ በበኩላቸው መንገድ ትራንስፖርት ካወጣው ታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ በመደረጉ ለወጪ መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ከታክሲ ተራ እስከ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ታሪፉ 5 ብር ቢሆንም በእጥፍ ጨምረው 10 ብር እንደሚያስከፍሏቸው ተናግሮ "ችግሩን ለሚመለከተው አካል ብናሳውቅም በጊዜያዊነት እንጂ በዘላቂነት ሊፈታልን አልቻለም" ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ በከተማው ባደረገው ምልከታ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ከተመን በላይ ከማስከፈላቸው በተጨማሪ ኮንትራት ካልሆነ በስተቀር አንሄድም በሚል ተገልጋዩን ሲያጉላሉ ማየቱን አረጋግጣል። በተለይ ዝናብ ሲጥልና ምሽት ከአንድ ሰዓት በኋላ አሽከርካሪዎች ያለኮንትራት ስለማይጭኑ ተሳፋሪዎች በእግር ለመጓዝ ሲገደዱ ማስተዋሉንም እንዲሁ፡ በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የትራንስፖርት ልማት ቡድን መሪ አቶ አስናቀ ከተማ በበኩላቸው ባለሦስት እግር ባጃጅ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ ዋጋ በማስከፈል ህብረተሰቡን እያማረሩ ስለመሆኑ ቢሮው መረጃ እንዳለው ገልጸዋል። የህዝቡን ቅሬታ በመቀበል የቁጥጥር ሥራ መጀመሩን ጠቁመው፣ በተያዘው ሳምንት ብቻ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማዎች በ26 የባጃጅ አሽከርካሪዎች ላይ በያንዳንዳቸው የ300 ብር ገንዘብ ቅጣትና የጽፉፍ ማስጠንቀቂያ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ እስከ መንጃ ፍቃድ እስከመንጠቅ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው አሽከርካሪዎች ከህገወጥ እንቅስቃሴያቸው ሊታቀቡና ህብረተሰቡን በቅንነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ አሳስበዋል። ለህብረተሰቡ ግልጽ በሆነ ቦታና የየአካባቢውን የትራንስፖርት ታሪፍ እንዲያውቅ በመደረጉ ህብረተሰቡ ያለአግባብ ክፍያ ሲጠየቅ ጥቆማ በማድረስ ለመብቱ መከበር ዘብ ሊቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ በመንገድና ትራንስፖርት ባለሙያዎች ብቻ የሚፈለገው ለውጥ ስለማይመጣ ሕብረተሰቡ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። የክትትልና የቁጥጥር ስራውም እንደሚጠናከር ነው የገለጹት። በከተማው ከ850 በላይ ባጃጆችና ከ75 በላይ የዳማስ ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸው ታውቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም