ከአተት በሽታ ህብረተሰቡን ለመታደግ ሆቴሎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው-ነዋሪዎች

73
አዲስ አበባ  ሰኔ 26/2010 ከክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ ከሚከሰት የአተት በሽታ ህብረተሰቡን ለመታደግ በተለይ ሆቴሎችና ምግብ ቤቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች አብዛኛውን ጊዜ የግልና የአካባቢን ንጽህና አለመጠበቅ ለአተት በሽታ መምጫ ሁነኛ መንስኤ መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለበሽታው እንዳይጋለጥ በማድረግ ረገድ በተለይም የሆቴሎች፣ የምግብ ቤቶችና አትክልት ቤቶች ሚናቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባም ነው የገለጹት። ኢዜአ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ተዘዋውሮ ባደረገው ምልከታ መሰረት ምግብ በሚሰሩባቸው አካባቢዎች ላይ ቆሻሻዎች ተጥለው ተመልክቷል። ምግብ ከማዘጋጀትና ከማቅረብ በፊት እንዲሁም ከመጸዳጃ ቤት መልስ ሁልጊዜ እጆቻቸውን በውሃና በሳሙና በደንብ በመታጠብ ለተገልጋዮች ጤና መጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል። የግልና የአካባቢን ንጽህና በመጠበቅ፣ ዝንቦች እንዳይራቡ በማድረግ እንደዚሁም ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ በተመደበለት ስፍራ ማስወገድ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። በዚህም ማንኛውንም ከቤት የሚወጣ ደረቅ ወይም ፈሳሽ ቆሻሻን ውሃንና አካባቢን በማይበክል መልኩ በአግባቡ ማስወገድ እንደሚገባም አክለዋል። የከተማው ነዋሪ ወጣት መቅደስ ጌታቸው በሰጠችው አስተያየት"ዕቃዎችን በጽዳት መያዝ፤  በምግብ ላይ  ጥንቃቄ ማድርግ ፤ ፍሪጅ ወስጥም ቢሆን ከጊዜ ያለፈበትን  አለማስቀመጥ፤ በአካባቢ ያለውን ቆሻሻ ማጽዳት " ያስፈልግል ብላለች፡፡  "ውሃ አጋር መጠቀም ፤ ምግብ  ሲሰራ እጃችንን ታጥቦ መስራት፣ አተት ለመከላከል  ይጠቅማል  "ያለችው ሌላዋ ነዋሪ ወጣት ትዝታ ሸዋንደነቀው ነች፡፡  ምግብ ቤቶች በበኩላቸው የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በሚያቀርቡት ምግብም ንጽህና በመጠበቅ እና ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነው የገለጹት። "በስራ ሂደታችን በቀን በቀን ያለውን ቆሻሻም እናስወግዳለን፤ የምግብ አገልግሎት አሰጣጣችንም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ነው ለከስተመር የምናቀርበው፤ ለምንሰራባቸው ነገሮችም በንጽህና ታጥቦና ተከድኖ ነው የሚቀመጠው ።" የሚሉት የጣዝማ ሆቴል ስራ አስኪያጅ  አቶ አያሌው ካሳሁን ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ ከየተቋማቱ የሚወጡ ቆሻሻዎችን በአግባቡ የሚሰበስቡ የግል የጽዳት ድርጅቶች ያሉ በመሆናቸው ቆሻሻዎችን የማይሰበስቡ ከሆነ ለኤጀንኢው ጥቆማ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ አቶ ይብሬ እስማኤል እንደገለጹት ቁጥራቸው 33 የሚሆኑ የግል የጽዳት ድርጅቶች ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ። በመሆኑም ድርጅቶቹ ስራቸውን በአግባቡ የማያከናውኑ ከሆነና ቆሻሻውን ማንሳት በሚገባቸው ወቅት የማያነሱ ከሆነ ለኤጀንሲው ጥቆማ መስጠት አንደሚገባቸውም ገልጸዋል። ህብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ እንዲሁም የበሰሉ አትክልቶችን በመመገብ ራሱን ከአተት በሽታ እንዲታደግም ነዋሪዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ኤጀንሲው በቀጣይ የተገልጋዮችን ፍላጎት ለማሟላትና አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ የሚረዳ የነጻ ጥሪና ሌሎች አገልግሎት አሰራርንም እንደሚጀምር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም