በደቡብ ክልል የ188 ተከሳሾች ክስ ተቋረጠ

68
ሀዋሳ ሰኔ 26/2010 የደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ የ188 ተከሳሾችን ክስ አቋረጠ። ቢሮው ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የተከሳሾች ክስ የተቋረጠው ከሰኔ 26 ቀን 2010 ጀምሮ ነው። በክልሉ ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ኮንሶ ወረዳ ሁከትና ብጥብጥ ተከስቶ እንደነበር አስታውሷል፡፡ ከሁከትና ብጥበጡ ጋር ተያይዞ ህገ መንግስታዊ ስርዓት በማፍረስ ሙከራና የስልጣን ተግባራዊነቱን በማሰናከል ወንጀል በርካታ ግለሰቦች  በምርመራ ተጣርቶ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ መንግስት በጥር ወር 2010 ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ክስ ተመስርቶባቸው በክርክር ሂደት ላይ የነበሩ 188 ተከሳሾችም ክሳቸው መቋረጡን በመግለጫው  ተመልክቷል፡፡ የተሸለ ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና በአገሪቱ የተጀመረውን የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የመደመር፣ የአንድነትና የለውጥ ሂደትን ለማስቀጠል ሲባል የተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ መወሰኑንም ነው  የተብራራው፡፡ በተጨማሪም ባለፉት ሦስት ወራት በአገሪቱ እየታየ ያለውን የለውጥ ጅማሮ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሲባል ቢሮው ከፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተሰጠው የውክልና ስልጣን መሰረት ክሱን አንስቷል፡፡ በእዚህም በከባድ የሰው ግድያ ወንጀል በተደራራቢነት ከተከሰሱት ሁለት ተከሳሾች በስተቀር በስምነት መዝገቦች የተከሰሱ 188 ሰዎች ክሳቸው መቋረጡንና ከእነዚህ ውስጥ ያልተያዙ መኖራቸውም ተመልክቷል፡፡ የክልሉ መንግስት ክሱ ቢነሳላቸው የህዝብና የመንግስት ጥቅም በተሸለ ሁኔታ ይጠበቃል ብሎ በማመኑም ጭምር ክሱ መቋረጡን በመግለጫው ተገልጿል፡፡ በቀጣይ ተከሳሾቹ ወደ ሕብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ጥላቻን በፍቅር በመተካት የጋራ በሚያደርጉ እሴቶች መሰረት ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካዊና የኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት መስራት እንዳለባቸውም ነው መግለጫው ያስገነዘበው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም