በአማራ ክልለ የተከሰተው የተምች ወረርሽኝ እንዳይዛመት ለመከላከል እየተሰራ ነው

56
ባህር ዳር ሰኔ 26/2010 በአማራ ክልል ከ36 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በተዘራ የበቆሎና የማሽላ ሰብል የተከሰተው የተምች ወረርሽኝ እንዳይዛመት የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። የቢሮው የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አሻግሬ እንዳየን ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ስድስት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 40 ወረዳዎች የተከሰተው   አሜሪካን መጤ ተምች በሌሎች አካባቢ እንዳይዛመት የመከላከል ሥራ ተጀምሯል። ከሰኔ 7 ቀን 2010ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተውን የተምች ወረርሽኝ ለመከላከል ቢሮው ከ14 ሺህ ሊትር በላይ የፀረ ሰብል ተባይ ኬሚካል በማቅረብ  ለዞኖች እያከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል። ዘንድሮ ተምች በአብዛኛው የተከሰተው ባለፈው ዓመት በክልሉ ባልታየባቸው የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜን ሸዋ እንዲሁም በደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች ውስጥ መሆኑንና በአካባቢዎቹ የተዘራውን የማሽላ ሰብልንም ማጥቃቱን አስረድተዋል። በምዕራብ ጎጃምና በደቡብ ጎንደር ዞኖችም የተምች ወረርሽኙ ዳግም ተከስቶ በበቆሎ ሰብል ቡቃያ ላይ ጥቃት ማድረሱንም ጠቁመዋል። "ተምቹ ከተከሰተ ጀምሮ እስካሁን በተደረገ የፀረ-ኬሚካል ርጭትና በባህላዊ መንገድ በእጅ ለቀማ ለመከላከል በተሰራው ሥራ በ5 ሺህ 841 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራን የበቆሎና የማሽላ ሰብል ከወረርሽኙ መከላከል ተችሏል" ብለዋል። ከሁለት ሺህ 150 ሊትር በላይ የተለያዩ የፀረ-ሰብል ተባይ ኬሚካሎችም ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል። በተምቹ የተወረረውን ቀሪ መሬትም የአርሶ አደሩን አደረጃጀት በመጠቀም በባህላዊ መንገድ  የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል  እንዲቀጥል አሳስበዋል። ዳግም የተቀሰቀሰው አዲሱ የተምች ወረርሽኝ በቀን እስከ 500 ኪሎ ሜትር የመብረር አቅም ያለው በመሆኑ ፈጥኖ መከላከል ካልተቻለ ሰብልን ሙሉ በሙሉ ሊያወድም እንደሚችልም ታውቋል። አቶ አሻግሬ እንዳሉት የተከሰተውን ፀረ ሰብል ተባይ ትኩረት ሰጥቶ ለመከላከል በየደረጃው ለሚገኙ ባለሙያዎችና ለአርሶ አደሩ የተጠናከረ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ ይገኛል። አርሶ አደሮች ተምቹ በማሳቸው ተከስቶ ሲገኝ በአካባቢያቸው ለሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ፈጥነው ማሳወቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ የብርሃኑ ንጋቱ የእርሻ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ አስተውል አትንኩት እንደገለጹት በ88 ሄክታር መሬት ላይ ከተዘራ የበቆሎ ቡቃያ ማሳ ውስጥ በአምስት ሄክታሩ ላይ ተምቹ ከአምስት ቀን በፊት መከሰቱን ገልጸዋል። ተምቹ ሁሉንም የበቆሎ ሰብል እንዳይወር ፀረ-ሰብል ተባይ ኬሚካል የመርጨትና በቀን ከ20 በላይ ሰራተኞችን በመቅጠር በባህላዊ ዘዴ   የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት በ10 ሄክታር መሬት ላይ በተዘራ የበቆሎ ቡቃያ ላይ ተምቹ ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው ትኩረት ተሰጥቶ በተሰራው ሥራ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል። ከሰኔ ሰባት ጀምሮ በ150 ሄክታር በተዘራ የበቆሎ ሰብል ላይ የተከሰተውን የተምች ወረርሽኝ የመከላከል ሥራ እያከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በእዚሁ ወረዳ የሶማ እርሻ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋሁን ሰውነት ናቸው። እስካሁንም ከ100 ሊትር በላይ የፀረ-ሰብል ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ በማዋልና በየቀኑ 200 የቀን ሠራተኞችን አሰማርቶ በእጅ የመልቀም ስራ በመሰራቱ ተባዩን ከ90 በመቶ በላይ መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል። ባለፈው ዓመት ከደቡብ ክልል የተነሳው “ፎል አርሚ ወርም” የተሰኘው የአሜሪካ መጤ ተምች ወረርሽኝ ወደ አማራ ክልል ተዛምቶ ከ114 ሺህ ሄክታር በላይ የተዘራ ሰብልን ቢወርም በተደረገ ርብርብ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉ ይታወሳል ሲል የገበው ኢዜአ ነው ።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም