ኢትዮጵያ ለብዝሃ ህይወት ዝርያዎች ተገቢ እንክብካቤ እያደረገች ነው

109
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2010 የኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከግብ ለማድረስ ለብዝሃ ህይወት ዝርያዎች ተገቢ እንክብካቤ እያደረገች መሆኑን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ ገለጹ። የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ከጀርመን መንግስት ባገኘው የ400 ሺህ ዩሮ ድጋፍ ያስገነባውን የ “ጀነቲክና ሆርቲካልቸር” ዝርያዎች ማቆያ ማዕከል ዛሬ አስመርቋል። የማዕከሉ ሙቀት ከዜሮ በታች 20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሲሆን 134 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው በውስጡ ያሉ የጀነቲክና የሆርቲካልቸር ዝርያዎችን ለረጅም ጊዜ ማቆየት ይችላል። የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ እንዳሉት፤ የብዝሃ ህይወት ዝርያዎች የአካባቢ ስነ ምህዳር ከመጠበቅ ባለፈ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ያላቸው ሚና የጎላ ነው። ኢትዮጵያ የዓለምን ሙቀትና የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ከብክለት ነጻ የሆነ ኢኮኖሚ በመገንባት ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። ለብዝሃ ህይወት ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ በመስራቅ አፍሪካ የብዝሃ ህይወት አስተዳደር የልህቀት ማዕከል በመሆን የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ማሰማራቷን ገልጸዋል። የኬንያ የብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ስልጠና ማግኘታቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ “በገንዘብ አቅርቦት በኩል ያለውን ውስንነት ለመፍታት ከተለያዩ አገሮች ጋር በቅንጅት እንሰራለን'' ብለዋል። ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የገባችውን ቃል ለመፈጸም ቁርጠኛ መሆኗን ለዓለም ማሳየቷን ዶክተር ገመዶ ተናግረዋል። የጀርመን መንግስት እአአ ከ1976 ጀምሮ ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በአካባቢ ስነ ምህዳር ጥበቃ ላይ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። “በዚህም ሙሉ የሰው ሃይልና መሳሪያውን በማስገባት ዘመናዊና እስከ 10 ዓመት የተለያዩ የጀነቲክና ሆርቲካልቸር ዝርያዎችን መያዝ የሚችል  ማቆያ ማዕከል አስገንብቷል'' ብለዋል። በቀጣይም የተሻሻሉ ዝርያዎቸን ለማፍራት፣ የካርበን ልቀትን በመቀነሰ የአረጓዴ ልማትን ለማምጣት ከጀርመን መንግስት ጋር በቅንጅት ለመስራተ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ምሪዮ ማዕከሉ ዝርያዎቹ እንደያዙት የእርጥበት መጠን ለብዙ ጊዜ ማቆየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። ይኸውም ቀድሞ ከነበሩት ባለ አራት እና ከዜሮ በታች ባለ 10 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የዘረመል ማቆያ ማዕከላት በጥራትም ሆነ በስፋት የተሻለ በመሆኑ ከአስር ዓመት በላይ ሳይበላሽ ይቆያል ብለዋል። በጀርመን መንግስት ሙሉ የገንዘብና የባለሙያ ድጋፍ የተገነባው ማዕከሉ ወደፊት በምርምር የሚደረስባቸውን ዝርያዎች በአግባቡ ለመያዝ የሚያስችል መሆኑን ዶክተር መለሰ ገልጸዋል። የጀርመን መንግስት ድጋፍ በማድረግ ማዕከሉን በማስገንባቱ ምስጋና አቅርበዋል። የጀርመን ምግብና ግብርና ሚኒስትር ፍሬድሪክ ዋከር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ዘላቂ የግብርና ምርታማነት እንድታስመዘገብ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል። “ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ማረጋገጥ እንድትችል የተሻሻሉ ዝርያዎችን መጠቀም ይኖርባታል'' ብለዋል። ጀርመን በግብርና ዘርፍ ከ40 ዓመት በላይ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት መስራቷን ያወሱት ሚኒስትሩ፤ “በቀጣይም በገንዘብ ድጋፍና በቴክኖሎጂ ሽግግር በቅንጅት እንሰራለን'' ብለዋል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን በመጠቀም ለአረንጓዴ ልማት በምታደርገው አስተዋፅኦ የጀርመን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም