ከ20 ዓመት በታች የአገር አቀፍ የቼስ ሻምፒዮና በድሬዳዋ ከተማ ተጀመረ

56
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2010 ሁለተኛው ከ20 ዓመት በታች የአገር አቀፍ የቼስ ሻምፒዮና ትናንት በድሬዳዋ ከተማ ተጀምሯል። እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች ከአራት ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ100 በላይ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። ደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና አማራ በሻምፒዮናው ላይ የሚሳተፉ ክልሎች ናቸው። የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለታዳጊዎች የውድድር አማራጭ መፍጠር በስፖርቱ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግና ተተኪዎችን ማፍራት የሻምፒዮናው ዋንኛ አላማ ነው። ተወዳዳሪዎቹ በሻምፒዮናው የሚያገኙት ልምድ ያለባቸውን ክፍተት በማየት ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል። አሸናፊ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ሌሎች የቼስ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ እድል እንደሚያገኙም አመልክተዋል። በአጠቃላይ ሻምፒዮናው በቡድንና በግል የበላይነት በሚሉ ዘርፎች እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል። የመጀመሪያው ከ20 ዓመት በታች የአገር አቀፍ የቼስ ሻምፒዮና ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የትግራይ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም