በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆናቸውን በድሬደዋ በአነስተኛ ስራ የተሰማሩ ሴቶች ተናገሩ

56
ድሬደዋ ሚያዝያ 29/8/2010 ተደራጅተውና በተናጠል እያካሄዱት ባለው የገቢ ማስገኛ የስራ ውጤታማ በመሆን ኑሯቸውን ማሻሻል እንደቻሉ በድሬደዋ አስተያየታቸውን የሰጡ በአነስተኛ  ስራ የተሰማሩ ሴቶች ተናገሩ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የተመራ ቡድን በድሬዳዋ አስተዳደር በመገኘት የሴቶችን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል፡፡ በአስተዳደሩ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል የኡሉል ሞጆ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ሀኒፋ ሞሊድ እንዳሉት ከሌሎች ሴቶች ጋር ተደራጅተው መንቀሳቀስ የጀመሩት ከ2002 ዓ.ም. ወዲህ ነው፡፡ በአደረጃጀታቸው በመታገዝ ባገኙት የገንዘብ ብድር አገልግሎት እንስሳት እርባታና ጥቃቅን የንግድ ሥራ ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ  የጋራ ወፍጮ ቤት እንዳላቸው  ተናግረዋል፡፡ " አሁን ላይ ሀብታችን 2 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር ደርሷል፤ በቀጣይ በተለያዩ ከፍተኛ የንግድ ሥራ ላይ መሳተፍ እንፈልጋለን፤ አመራሮችም ገጠር መጥታችሁ ሥራችን ማየታችሁ ያነቃቃናል"ብለዋል፡፡ " ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በወሰድኩት ጥቂት ገንዘብ በመነሳት አሁን የግሮሰሪና የሚኒባስ ባለቤት ሆኛለሁ " ያሉት ደግሞ የከተማ ዜሮ አምስት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አለም አይናለም ናቸው፡፡ በቀጣይ በራሳቸው ፈጠራ በሙከራ ደረጃ እያመረቱ የሚገኙትን ልዩ ልዩ የአልኮል መጠጥም እውቅና ከተሰጣቸው ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪ  ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ የሊዝ ማሽን ግዥ በልማት ባንክ በኩል ከተመቻቸላቸው ዓላማቸውን በአጭር ጊዜ እንደሚያሳኩ  ለቡድኑ አስታውቀዋል፡፡ ህብረት ለልማት የደረቅ ቆሻሻና ፍሳሽ አስወጋጅ የህብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሄለን ግርማ በተናቁ ስራዎች ተሰማርቶ ህይወትን መለወጥ እንደሚቻል በተግባር ማሳየታቸውን ተናግራለች፡፡ ፡ "57 አባላት አሉን ፤330 ሺህ ብር ቆጥበናል፤ በ120 ሺ ብር የመታጠቢያና የመጸዳጃ ቤት አሰርተን አገልግሎት እየሰጠን ነው፤ በቀጣይ የራሳችን የቆሻሻ መኪና በመግዛትና ቆሻሻውን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት በመለወጥ ለገበያ ማቅረብ ይሆናል" ብላለች፡፡ በስደት አረብ ሀገር ቆይታ በመመለስ በከተማ ግብርና የተሰማራችው ወጣት እቴቱ ወንድወሰን በበኩሏ የተመቻቸላትን የብድር ገንዘብ ተጠቅማ ምርጥ የአበባ ችግኞች በማፍላት ለደንበኞቿ እያቀረበች ውጤታማ መሆኗን ገልጻለች፡፡ ወጣቷ እንዳለችው ከምንም በመነሳት አሁን ላይ የባጃጅና የ180ሺህ ብር ባለቤት መሆን ችላለች። መንግስት ያለባቸውን የቦታ፣ የመሸጫና የማምረት ችግሮች ከፈታላቸው ስራቸውን አሻሽለው በማስፋት ለሌሎችም ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል፡፡ የሴቶቹን የስራ እንቅስቃሴ የተመለከቱት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በከፍተኛ የስልጣን ዕርከን ከተሾሙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በድሬዳዋ ባደረጉት የሥራ ጉብኝትና በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ በድሬዳዋ ሴቶች በቁርጠኝነት የሚያከናውኗቸው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የአስተዳደሩ አመራርና ሙያተኞች ሴቶችን ለማገዝ የሚተገብሯቸው እቅዶችን በማስፋት፤ ያሉባቸውን የመስሪያና መሸጫ ክፍተቶች በማስተካከል የተሻለ ለውጥ እንዲያመጡ መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋዬ በበኩላቸው ውጤታማ ሴቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሸጋገሩ መንግስት ባመቻቸላቸው የማሽነሪ ሊዝ ግዥ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡ "ከድሬዳዋ የተገኘው ምርጥ ተሞክሮ በመስፋት ለሌሎችም እንዲያገለግል ይደረጋል "ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም