ህዝበ ክርስትያኑ በዓሉን ሲያከብር ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ ቀረበ

51

ሀዋሳ ፣ሚያዝያ 8/2012 (ኢዜአ) ህዝበ ክርስትያኑ የስቅለትና የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ ቀረበ ።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በዓሉን በማስመልከት ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ጥረት ህዝበ ክርስትያኑ በዓሉን በቤቱ በማክበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት።

መንግስት በአሁኑ ወቅት በሽታውን ለመከላከል ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በመተግበር ህዝቡ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ከአራት ሰው በላይ በአንድ ቦታ መሰብሰብ የሚከለክለውን መመሪያ በመተግበር በስግደት ወቅት ከአካላዊ ንክኪ በመራቅ የቫይረሱን ስርጭት እንዲከላከል መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል።እንደ መንግስትም ተገቢውን ድጋፍ እናደርጋለን ያሉት አቶ ርስቱ የጸጥታ ኃይሉም ህግ የማስከበር ስራውን እንደሚያከናውን  አስታውቀዋል።

ከበዓሉ ጋር በተያያዘ በገበያ ስፍራ መጨናነቅ እንዳይከሰት ቀደም ሲል በአንድ ቦታ ይካሄድ የነበረውን በተለያዩ ስፍራዎች በመከፋፍል እንዲካሄድ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።።በግብይት ወቅት ህብረተሰቡ ርቀትን በመጠበቅና እጅን በመታጠብ ከንክኪ ነጻ በሆነ መልኩ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን በበዓል ወቅት በመሰባሰብ በጋራ የማክበር ልምድ እንዳላቸው ያወሱት  አቶ ርስቱ ወቅቱ በጋራ ተሰባስቦ የሚከበርበት ሳይሆን በአካል ተራርቆ በመንፈስ አንድ ሆኖ ማክበር እንደሚገባ አመልክተዋል።

"ረዳትና ደጋፊ የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን በማካፈል  ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለብን "ብለዋል።

አቶ ርስቱ ለመላው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላምና የጤና እንዲሆንላቸው  መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም