የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊና ወቅታዊ ነው...የህግ ምሁራን

73

ባህርዳር ሚያዚያ 8/2012 (ኢዜአ) መንግስት የኮሮና ቫይረስን ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የማስፈጸሚያ ደንብ ማውጣቱ ወቅታዊና አስፈላጊ ነው ሲሉ የባህርዳር ዩንቨርሲቲ የህግ ምሁራን ገለጹ።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የህግ አገልግሎት ዳይሬክተርና መምህር አቶ ደሳለኝ ጥጋቡ ለኢዜአ እንደገለጹት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮሮና ቫይረስን በመከላከል የአገራችን ህዝብ ህይወት ለመታደግና የአገር ህልውና ለማስቀጠል የሚያስችል ነው።

በኢኮኖሚ አቅማቸው የዳበሩና ጠንካራ የጤና ስርዓት የገነቡ አገራት አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያደረሰባቸው የሚገኘውን እልቂት መቋቋም አልቻሉም።

"አብዛኛዎቹ አገራት የአስቸኳይ ጊዜ በማወጅ የህዝባቸውን መብቶች በመገደብ የዜጎቻቸውን ህይወት ለማትረፍ ጥረት እያደረጉ የሚገኙበት ወቅት ላይ እንገኛለን" ብለዋል።

የአገራችን መንግስትም የኮሮና ቫይይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ማስፈጸሚያ ደንብ ማውጣቱ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ መሰረታዊ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን መደረግ የሌለባቸውን ጉዳዮች የሚከለክሉና ግዴታን የሚጥሉ ሃሳቦች የተካተቱበት በመሆኑ በአግባቡ ተገንዝቦ መፈጸም ይገባል።

የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ካለን የተሳሰረ የማህበራዊ አኗኗር ጋር ተያይዞ የመንቀሳቀስና የንብረት መብቶችን ብቻ እንጂ ሌሎች በህገ መንግስቱ የማይሸረሸሩና የማይገደቡ መብቶች ጋር የሚጣረስ አይደለም ብለዋል።  

የተከለከሉ ጉዳዮችን ባለማድረግና ግዴታዎችን በመፈጸም ህብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የኮሮና ቫይረስን መከላከል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ተገኘ ዘርጋው እንዳሉት ደግሞ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥምና ወረርሽኝ ሲከሰት መሆኑን ይደነግጋል።

በዚህ መሰረትም የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ብሎ ይፋ ያደረገው በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው መሆኑን በመገንዘብ መተግበር ግዴታ መሆኑን አስረድተዋል።

የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ማስፈጸሚያ ደንቡን በመተግበር በሽታውን በመከላከልና ጉዳቱን በመቀነስ አኩሪ ድል ማስመዝገብ የወቅቱ ፈተና ነው ብለዋል።

የአገራችን ህዝቦች በመጀመሪያ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመጠበቅ ሲሉ  አዋጁን በማክበርና ለተፈጻሚነቱ ተባባሪ በመሆን የኮሮና በሽታን መከላከል እንዳለባቸው አሳሰበዋል።

“ምሁራንም ጥራት ያላቸው የመከላከያ ቁሳቁሶችን በማምረት፣ ጥናትና ምርምር በማካሄድ፣ የሌሎች አገሮች ተሞክሮን በማምጣት፣ በግንዛቤ ፈጠራና በተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ የራሳችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም