መምህራን ተማሪዎች ከትምህርት ነክ ጉዳዮች እንዳይለዩ ማበረታታትና መደገፍ ይጠበቅባቸዋል - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር

108

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2012 (ኢዜአ) መምህራን ተማሪዎች ከትምህርት ነክ ጉዳዮች እንዳይለዩ ማበረታታትና መደገፍ እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ።

መምህራን የኮሮናቫይረስን አስመልክቶ በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እንዲሳተፉ ጥሪውን አቅርቧል። 

መንግስት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከመጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ለኢዜአ በላከው መግለጫ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው በኢትዮጵያ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የትምህርት ማህበረሰብ አባላት የገጽ ለገጽ ትምህርት ማቆማቸውን ገልጿል።

መምህራንም የመማር ማስተማር ስራው ወደ ተለመደው ሁኔታ እስኪመለስ ድረስ ተማሪዎች ከትምህርት ነክ ጉዳዮች እንዳይለዩ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች የሚሰራጩ የትምህርት አቅርቦቶችን እንዲከታተሉ ማበረታታትና መስራት እንደሚገባቸው አመልክቷል።

መምህራን በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ሁኔታ ኢትዮጵያ የምታስተላልፋቸውን አገራዊ ጥሪዎች ተቀብለው ህብረተሰቡን የማገልገል ተግባር ማከናወናቸውን ነው ማህበሩ በመግለጫው ያወሳው።

በአሁኑ ጊዜም ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመሆኗ የመምህራን ተመሳሳይ ተሳትፎ በሚፈለግበት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስታውቋል።

መምህራን ተማሪዎቻቸውንና የአካባቢያቸውን ህብረተሰብ በተለያየ መልኩ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ እንዲያግዙ ማህበሩ ጥሪውን አቅርቧል።

በጤና ባለሙያዎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጡትን መልዕክቶች መምህራን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባቸው አሳስቧል።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት በዓለም ደረጃ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ተማሪዎች የገጽ ለገጽ ትምህርት ማቆማቸውን ትምህርት ዓለም አቀፍ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም