አዋጁን አክብሮ መተግበር ለራስ ነው !

71

እንግዳው ከፍ ያለው ባህርዳር

በቻይናዋ ውሃን ከተማ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወይም  ኮቪድ-19 በሽታ በዓለም በሚገኙ ሰባት አህጉራትን በማዳረስ ለሰው ልጆች ሞት፣ ህመምና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ማድረስ ከጀመረ ወራትን አስቆጥሯል።

ሚያዚያ 02 ቀን 2012 ዓ.ም በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ አንድ ኢትዮጵያዊን ጨምሮ 6 ሺህ 70 ሰዎች በዓለም ደረጃ በኮሮና ቫይረስ መሞታቸው በተለያዩ የዓለም ሚዲያዎች መነገሩ ይታወሳል ።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የስርጭት አድማሱን በማስፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ  1 ሚሊየን 938 ሺህ 840   ህዝብ በኮሮና ቫይረስ ሲያዝ  የሟቾች ቁጥር 120 ሺህ 857  እንዲደርስ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እያስከተለ ይገኛል።

የዓለም መንግስታትም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በቤት ውስጥ መቀመጥ፣ ጭንብልና ጓንት ማድረግ፣ ርቀትን ጠብቆ መንቀሳቀስ  የመሳሰሉት አስገዳጅ አዋጆችን በማውጣት ዜጎቻቸው ከበሽታው ለመጠበቅ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያም በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ መርሆዎችን እንዲተገበሩ  መንግስት  አዋጅ እስከ ማውጠት ደርሷል። የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነው ።

ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ እያደረሰ ካለው ሁለንተናዊ ምስቅልቅል  አንጻር ሲታይ ህዝባችን የኮሮና ቫይረስን መከላከል ካልተቻለ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ በውል የተገነዘበው አይመስልም።

ለዚህም እኛ ሃገር አይገባም። እምነታችን ይጠብቀናል። ጥቁሮችን አይዝም የሚሉና ሌሎች ውሃ የማይቋጥሩ አሉታዊ ሃሳቦች በምክንያትነት ሲነገሩ ይሰማል።

በኖርዌይ አገር የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን የሚከታተለው ዮሃንስ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጸው ኖርዌይን ጨምሮ በአውሮፓ የሚገኙ አንዳንድ አገራት እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ህዝባቸው በኮሮና ቫይረስ እንደሚያዝ በትንበያ ደረጃ አስቀምጠዋል።

እነዚህ አገራትም ወረርሽኙ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ እንዳይከሰትና ሰው የህክምና እርዳታ ሳያገኝ እንዳይሞት ግብ አስቀምጠው ርብርብ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

ኢትዮጵያም ከእነዚህ አገራት ተሞክሮ በመውሰድ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ በመሆን እልቂት እንዳያስከትል የአስተምህሮ ዘይቤዎችን ለእያንዳንዳንዱ  የህብረተሰብ ክፍሎች  በሚመጥን መልኩ መልዕክቶችን በመቅረጽ ማስተማርና ሌሎች የዝግጅት ምዕራፎችን መከወን እንዳለባት አሳስቧል።

በዚህም የአስም፣ የልብና ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዘ ህመም ያለባቸውና እድሜያቸው የገፋ ሰዎች በምንም አይነት መልኩ ከቤታቸው እንዳይወጡ ተከታታይ ትምህርት በመስጠትና ገደብ በማስቀመጥ  በሽታው የሚያስከትለውን ምስቅልቅል መቀነስ ይቻላል።

በተጨማሪም የፊት መሸፈኛ ጭንብል መንግስት ማቅረብ ካልቻለ አሰራሩን  በቴሌቪዥን በማሳየት ሁሉም ሰው የፊት ማስክ በቀላሉ በቤቱ አዘጋጅቶ እንዲጠቀም ማስተማር ያስፈልጋል።

ይህን ማድረግ ከተቻለ የህክምና ክትትል የሚያስፈልገው ታማሚ ቁጥር ውሱን ስለሚሆን የሃገሪቱ ሃኪሞች ታማሚዎችን አክሞ ለማዳንና በሽታው የሚያደርሰውን ሞት በቀላሉ ለመቀነስ አይከብዳቸውም የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ ጊቢ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ደረጀ ነገደ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስን በመከላከል መንግስት ያሳየው ተነሳሽነት ተቀባይነት ያለው ቢሆንም በህዝቡ የተስተዋለው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል ያሰጋል ብለዋል።

 “ቫይረሱ በኢኮኖሚና ማህበራዊ አቅማቸው ያደጉ እንደ አሜሪካ ያሉ ሃገራት በርካታ ዜጎችን በየቀኑ እየገደለ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እኛ ካለን ባህላዊና ሃይማኖታዊ መስተጋብራችን አንጻር ሲታይ ስጋቱ የሚያል መሆኑን መገመት አያዳግትም” ብለዋል።

የኮሮና በሽታ ከህክምና ውስብስብነትና ከሚያስከትለው ቀውስ አንጻር ብቸኛው መፍትሄ እጅን በሳሙና በየጊዜው መታጠብ፣ የፊት መሸፈኛ/ማስክ/ ማድረግና ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅን እንደእኛ ላሉ ታዳጊ አገራት ተመራጭ መፍትሄ መሆኑንም ጠቁመዋል።

“መንግስት የኮሮና መከላከል የሚያስችል አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት አጸድቆ ማውጣቱ የሚያስመሰግነው ቢሆንም ህብረተሰቡ መመሪያውን በመተግበር ህይወቱን የማትረፍ ሃላፊነቱን የመወጣቱ ጉዳይ አጠያያቂ መሆኑ ካለፉት ሳምንታት እንቅስቃሴ መረዳት ይቻላል።

“በእኛ ደረጃ 25 ምሁራን በአንድ ላይ ተሰባስበን ኮሚቴ በማዋቀር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቀመር ከመፍትሄው ጋር ለአማራ ክልል ግብረ ሃይል እያቀረብንና በቅርብ የምናገኛቸውን ሰዎች  በማስተማር ሃላፊነታችን እየተወጣን እንገኛለን” ብለዋል።

በየአካባቢው ያሉት ምሁራንም የተደረገውን አገራዊ ጥሪ በመቀበል ህዝቡን በማስተማር፣ ድጋፍ በማድረግ፣ ሳይንሳዊ ምርምር በማካሄድና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በማምጣት በኮሮና ቫይረስ  መከላከል አሻራቸውን ማሳረፍ ይጠብቅበቻዋል።

በተለይም ባለሃብቱና ህብረተሰቡ በገንዘብ፣ የምግብ እህል በማቅረብ፣ የንጽጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በመለገስ፣ የለይቶ ማቆያ ቤቶችን በመስጠትና ሌሎች ድጋፎች በማድረግ እያሳየ ያለውን የነቃ ተሳትፎ በምርምር በማስደገፍ በታሪክ ተመዝግቦ ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ የምሁራን ሚና ነው ብለዋል።

ምሁራኑ እንደሚሉት ህብረተሰቡ መንግስት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማክበር ፣ የጤና ባለሙያዎችና የሃይማኖት አባቶች የሚሰጡትን ምክር ሰምቶ መተግበር ጥቅሙ ለራስ መሆኑን ተገንዝቦ እንዲተገብረው መክረዋል ።

በኢትዮጵያም እስከ ሚያዚያ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 82 መድረሱንና የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን  የጤና ሚንስቴሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም