የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት እየተዘረጋ ነው

66

አዲስ አበባ ሚያዚያ 6/2012 በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሊያስከትል የሚችለውን ጫና ለመቀነስና የበሽታውን ስርጭት መቆጣጠር የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ኮቪድ 19ን ለመቆጣጠር በመንግስት ከተቋቋሙት ግብረኃይሎች መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ ግብረሃይል በሚኒስትር ምስሪያ ቤቱ እየተመራ ይገኛል።

ግብረ ኃይሉም እስካሁን የመንግስት እርምጃዎችን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

እስካሁንም በወረርሽኝ ስርጭት ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ቴክኖሎጂያዊ በሆነ መልኩ መፍትሔ ለመስጠት አራት የተሳሰሩ የትኩረት ዘርፎችን ለይቶ እየሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ ለኢዜአ የላከው መግለጫ አመልክቷል።

አንድኛው የትኩረት መስክ ዓለም አቀፋዊና አገር አቀፍ የተቀናጀ የኮቪድ 19 የመረጃ አሰጣጥ ስርዓት ዝርጋታ ነው።

አገልግሎት ሰጪ እና አገልግሎት ተቀባይ ባሉበት ሆነው አገልግሎት መስጠት እና መቀበል ማስቻል እንዲሁም አገራዊ የዲጂታል የክፍያ ስርዓትን አሟጦ መጠቀም ሌሎች የትኩረት መስክ መሆኑ ተገልጿል።

በመማር ማስተማር ስርዓቱ ውስጥ ተማሪዎች በቤታቸው ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻል ሌለኛው የትኩረት መስክ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

የመረጃ አሰጣጥ ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግም በጤና ሚኒስቴር በኩል COVID19.et  የተሰኘ የተቀናጀ የመረጃ መለዋወጫ ስርዓት በልጽጎ ስራ ላይ መዋሉ ታውቋል።

ስርዓቱ ኮቪድ 19 የተመለከቱ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ሁኔታዎች የሚያሳውቁ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ ማጠናቀር እና ማሰራጨት የሚያስችል ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ዜጎች መረጃ የሚሰጡበት፣ አገራዊ ሀብትን በአግባቡ ለማስተዳደርና ለመምራት የሚያስችሉ መተግበሪያዎች/አፕሊኬሽኖች/ የተካተቱበት ነው ተብሏል።

የተዘረጋው ስርዓት እንደ ፌስ ቡክ፣ ሚሴንጀር፣ ዋትስ አፕ፤ ቴሌግራምን የመሳሰሉ ማሕበራዊ ሚድያ መጠቀሚያ ፕላትፎርሞችን አስተሳስሮ የያዘ መሆኑ ተገልጿል።

በተመረጡ ርዕስ ጉዳዮች ላይም ማሕበረሰቡ መረጃ እንዲጠይቅና ምላሽ እንዲያገኝ የሚያስችሉ 'ቻት ቦቶች' ተሰርተው ተካተውበታል ተብሏል።

ከዚህ ጎን ለጎን የጥሪ ማዕከሎች በፌደራል እና በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የቴክኖሎጂ አማራጮች ተለይተው በ34 የመንግስት መስሪያ ቤቶች በ176 አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ እንዲደፉም ተደርጓል ነው የተባለው።

ለዚህ ደግሞ የeservices.gov.et የተሰኘ የአገልግሎት መስጫ ፖርታል ስራ ላይ መዋሉን የጠቀሰው መግለጫው ተገልጋዮች የአገልግሎት ክፍያም በባንክ በኩል እንዲፈጽሙ ዕድል የሰጠ ነው።

የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት ስብሰባዎችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ በመጠቀም ውይይቶችና ስብሰባዎችን እንዲያካሄዱ ድጋፍ የማድርግ ስራ መሰራቱም ታውቋል።

በዲጂታል ክፍያ ዘዴዎች ለመጠቀም እንዲቻል አገራዊ የዲጂታል የክፍያ ስረዓት አማራጮችን ተግባራዊ የማድረግ ስራም ተከናውኗል ነው የተባለው።

እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶችም ቫይረሱ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የሆነውን አካላዊ ንክኪ በመቀነስ ያስቻሉ መሆናቸውም ተገልጿል።

ግብር ኃይሉ በስራዎች ላይ ማነቆ ሆነው የቆዩ ሕጎችም በፍጥነት እንዲሻሸሉ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ በሚንስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ተልኳል ነው የተባለው።

አዋጁ ሲጸድቅ የግል የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እና አገልግሎት አቅራቢዎች ወደ ዘርፉ ገብተው የፋይናንስ ስርዓቱን ማገዝ፣ ማስፋት እና ማሳደግ እንዲችሉ ያግዛልም ተብሏል።

በቀጣይም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸውና ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የሕበረተሰብ ክፍሎችን የሚግዝ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

ተማሪዎችም በቤታቸው ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በክልሎች በየቋንቋቸው ትምህርት በሬዲዮ እንዲጀምርም መደረጉ ተገልጿል።

ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የትምህርት ቴሌቪዥን ቻናል ተጠቅሞ እና ለከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ኮርሶችና ዋቢ መጻህፍቶች 'በኦንላይን በዲጅታል ላይብረሪ'ና ኦንላይን ትምህርት መስጫ ዘዴዎችን መጠቀም በተመረጡ ዩንቨርስቲዎች ትግበራው ተጀምሯል።

ለኮቪድ 19 የጥሪ ማእከሎቹም በፌዴራል 8335 እና 952፤ በኦሮሚያ 6955፣ በአማራ 6981፣ በትግራይ 6244፣ በሶማሊ 6599፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች 6929፣ በሀረሪ 6864፣ በዓፋር 6220 ናቸው።

በጋምቤላ 6184፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ 6016፣ በአዲስ አበባ 6406 እና በድሬዳዋ 6407 በጥቅሉ 11 የጥሪ መዕከላት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም