ህግ አስከባሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሲያስፈፅሙ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን እንዲያከብሩ ተጠየቀ

93

አዲስ አበባ ሚያዚያ 6/2012(ኢዜአ) የህግ አስከባሪ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚያስፈፅሙበት ወቅት በሰብዓዊ መብቶች እና ሕገ-መንግሥታዊ መርሆች ላይ ተመስርተው ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን አዋጁ የሚያስፈጽሙ ሁሉም የሕግ አስከባሪ አካላት እና አስፈፃሚ ተቋማት በአፈፃፀም ሂደት ሊከተሏቸው ስለሚገቡ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች፣ መርሆች እና ግዴታዎችን አስመልክቶ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

በእዚህም የኮቪድ-19 (የኮሮናቫይረስ) ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ መንግስት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

አዋጁን የሚያስፈጽሙ አካላትና ተቋማት በማናቸውም ሁኔታ በሕገ-መንግሥቱ እና በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሠረት ሊገደቡ የማይችሉ መብቶችን እንዲያከብሩ፣ እንዲያስከብሩና በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና በሙያዊ ሥነ-ምግባር እንዲመሩ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

መሰረታዊ የሚባሉ በሕይወት የመኖርና መሰል መብቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊገደቡ እንደማይገባ ገልጾ ሙሉ በሙሉም የማክበር እና የማስከበር ግዴታዎች መቀጠል እንዳለባቸው አሳስቧል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የፖለቲካና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ጊዜያዊ እገዳ ሊደረግ እንደሚችልም ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚወሰዱ የአፈጻጸም እርምጃዎችን እንደሚከታተልም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

እንደኮሚሽኑ መግለጫ በአዋጁ አፈጻጸም ላይ የሕግ አስከባሪ አካላት ልዩ ሚና እና ኃላፊነት አለባቸው።

መሠረታዊ መብቶች እንዳይጣሱ የመከላከል፣ ሊገደቡ የማይችሉ መሠረታዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ብሎም የአስቸኳይ ጊዜ ደንቡ በሕግ በተቀመጠለት ገደብ ልክ ሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ የሕግ አስከባሪ ተቋማት ሚና መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የሕግ አስከባሪ ተቋማት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና ዓላማውን ሲያስፈፅሙ ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ማስከበር የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡም ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው አዋጁን ተከትሎ የወጣውን ደንብ መተላለፍና ሌሎችንም ጥፋቶች የማጣራትና በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ሊቋረጥ የማይገባ ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሕግና ሥርዓትን እንዲሁም ከጤና ባለስልጣኖች የሚሰጡ መመሪያዎችን በማክበር የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እና ጉዳቱን ለመቀነስ የበኩሉን እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም