የአክሱም ዩኒቨርስቲ ያስገነባው የፍሳሽ ቆሻሻ የማጣሪያ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ

55
አክሱም ሰኔ 25/2010 የአክሱም ዩኒቨርስቲ 84 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ያስገነባው የፍሳሽ ቆሻሻ የማጣሪያ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ። የማጣሪያ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል ከዩኒቨርስቲው አጥር ግቢው የሚወጣውን ፍሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ ለማስወገድ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው  ዩኒቨርስቲው ገልጿል። በዩኒቨርስቲው የፕሮጀክቱ ኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ጽጌ ታፈራ ለኢዜአ እንዳሉት፣ፕሮጀክቱ ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ቦታዎች ያለአግባብ የሚፈስ ቆሻሻን ተሰባስቦ በዘመናዊ ማሽን እያጣራ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው። ከዩኒቨርሲቲው አጥር ግቢ በሚወጣው የፍሳሽ ቆሻሻ ምክንያት የአካባቢው አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይቷል። የማጣሪያ ፕሮጀክቱ አገልግሎት መሰጠት ከጀመረ ወዲህ በአርሶ አደሮች  ማሳ ላይ ይደርስ የነበረው ጉዳት፣  ፍሳሹ በሚፈጥረው መጥፎ ጠረንና የአየር ብክለት ምክንያት በአካባቢው ህብረተሰብ ሲያደርስ የቆየውን የጤና ችግር መከላከል መቻሉን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ የተጣራ ውሃ ለመስኖና ለግንባታ  ስራዎች ጥቅም እየሰጠ ነው። "በተጨማሪ ለመስኖ ልማት አገልግሎት የሚውልና የአፈር ለምነትን የሚጨምር ኮምፖስት /የተፈጥሮ ማዳበሪያ/  ለማምረት ድጋፍ እያደረገ ነው "ብለዋል። በ2004 በጀት ዓመት ግንባታው ተጀምሮ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው ፕሮጀክቱ  ጥቅም እያስገኘላቸው መሆኑን በዩኒቨርስቲው አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደር በርሄ አሰፋ ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት ከዩኒቨርስቲው አጥር ግቢ  ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይፈስ በነበረው ፍሳሽ ቆሻሻ ምክንያት በየዓመቱ በሰብላቸው ላይ ጉዳት ሲያደርስባቸው ቆይቷል። በችግሩ ምክንያትም በቂ ምርት ለመሰብሰብ ሲቸገሩ እንደቆዩና የጤናም ችግር ሆኖባቸው እንደነበር  አርሶ አደሩ አስታውሰው፣"ፕሮጀክቱ ስራ በመጀመሩ ምክንያት ሲደርስባቸው የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል "ብለዋል። በተጣራው ውሃ ማሳቸውን በመስኖ ማልማት እንደጀመሩም አርሶ አደሩ ጠቅሰዋል። አርሶ አደር እልፍነሽ ይሕደጎ በበኩላቸው፣ ላለፉት ዓመታት ከዩኒቨርሲቲው በሚወጣው ፍሳሽ ቆሻሻና በሚፈጥረው መጥፎ ጠረን ለመተንፈሻ አካል በሽታ ተዳርገው እንደነበር አስታውሰዋል። " የአካባቢው ማህበረሰብ ችግር ተረድቶ ዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ አስገንብቶ ለአግልግሎት ማብቃቱ ተገቢ ነው፣እኛ አርሶ አደሮች የነበረን ከፍተኛ ስጋት አስወግዶልናል" ያሉት ደግሞ ሌላ አርሶ አደር ኪዳነ ባህታ ናቸው። ከዚህ ቀደም  ማሳው በቆሻሻ እየተሞላ ማልማት ሳይችሉ መቆየታቸውን  ጠቅሰው ፣ አሁን በተሰራው የማጣሪያ ፕሮጀክት ቆሻሻን ከመከላከል አልፈው ማሳቸውን እያለሳለሱ በመስኖ ለማልማት ጭምር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም