የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ የክፍያ ስርዓት ይፋ አደረገ

1050

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2012(ኢዜአ) የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድህረ- ክፍያ ተጠቃሚዎች የወርሃዊ ፍጆታ ሒሳባቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኦንላይን ዲጂታል ክፍያ ስርዓት መፈጸም እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።

የኦንላይን ዲጂታል ክፍያ የወቅቱን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመከላከልም ባለፈ ወደ ዲጅታል ስርዓት የሚደረገውን ሽግግርም ያፋጥናል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሒሳብ ክፍያ ስርዓትን በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ካሉት 3 ነጥብ 2 ደንበኞቹ 2 ነጥብ 5 የሚሆኑት የድህረ – ክፍያ ተጠቃሚዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ እንዳሉት፤ ዜጎች ሒሳባቸውን በኦንላይን ዲጂታል ስርዓት ከቤታቸው ሆነው የሚፈጽሙበት ስርዓት ተዘርግቷል።

የኦንላይን ዲጅታል የክፍያ ስርዓቱ የደንበኞችን ጊዜና ጉልበት ከመቆጠብም ባለፈ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

አገልግሎቱ አምስት የክፍያ አማራጮች እንዳሉት የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚው በጥሬ ገንዘብ ከሚከናወነው ክፍያ ውጭ ሁሉም የደንበኞችን በአካለ መገኘት አይጠይቁም ብለዋል።

ከሂሳብ ተቀንሶ የሚፈፀም ክፍያ ከሂሳብ ወደ ሂሳብ ማስተላለፊያ ፎርም ለመሙላት ብቻ ከተገኙ በቂ መሆኑንም ገልጸዋዕል።

በቀጥታ ከሂሳብ ተቀናሽ ማድረግ፣ የሲቢኢ (CBE Birr) አገልግሎት እና የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ ደንበኞች ከቤታቸው ሆነው በቀለሉ በስልካቸው ክፍያ የሚፈጽሙባቸው አማራጮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አሰራሩ ጥር ላይ ተግባራዊ መደረግ እንደጀመረ የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚው ደንበኞች ከሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ ብለዋል።

ኢንዱስትሪዎችን የሚያንቀሳቅሱ ትላልቅ ባለሃብቶች አንድ ጊዜ ብቻ የክፍያ ፎርሙን ከሞሉ በቂ በመሆኑ በደንበኞች ዘንድ መጨናነቅ አይኖርም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ዮሐንስ ሚሊዮን ባንኩ ያለውን ተደራሽነት ተጠቅሞ ቀልጣፋ የኦንላይን አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

“በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ የኦንላይን ዲጂታል አገልግሎት ስርዓቱ የኮሮናቫይረስን ከመከላከልም ባለፈ ወደ ዲጂታል ስርዓት ለሚደረገውን ሽግግር አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

አብዛኛዎቹ የድህረ ክፍያ ተጠቃሚዎች የኦንላይን ስርላቱን መጠቀመ ከቻሉ ቀሪዎቹ ወደ ባንኩ በመሄድ ክፍያ ቢፈፅሙም መጨናነቅ እንደማይፈጠር ገልጸዋል።