ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ሁሉም የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ

91

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 2/2012(ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም የበኩሉን አስተዋፆና ትብብር እንዲያደርግ አሳሰቡ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ተኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ተኛ ልዩ ስብሰባው  በሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያወጣውን አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

የፀደቀውን አዋጅ አስመልክቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ መግለጫ ሰተዋል።

አፈጉባኤው በመግለጫቸው፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 መሰረት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጀ ማውጣቱን ተከትሎ ምክር ቤቱም ማጽደቁን ተናግረዋል።  

የጸደቀው አዋጅ መተኪያ የሌለውን የሰው ልጆች ህይወት ለመታደግ ከተለመደው አሰራር በመውጣት የሁሉም ርብርብ የሚደረግበት አሰራር መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ልብ ቆሞ ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከልና የሰዎችን ህይወት ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ለአዋጁ ተፈፃሚነት ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የአመለካከትና የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን ወደ ጎን በመተው የአገርና ህዝብ ህልውና የሚቀድም በመሆኑ በአንድነት መቆም ያስፈልጋልም ብለዋል።

በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የወረሽኙን ስርጭት ለመከላከልና ጉዳት ለመቀነስ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አካላትንም አፈ ጉባዔው አመስግነዋል።

የእምነት ተቋማትና መሪዎቻቸው ተከታዮቻቸውን ለማስተማርና ለማስገንዘብ እያደረጉ ያሉትን ጥረት አድንቀዋል።

ህዝቡ በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክርና መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርግ የጠየቁት አፈ ጉባዔው ይበልጥ ጥንቃቄ ማድርግ እነደሚያስፈልግ መክረዋል።

በስራ አካባቢዎችና የግብይት ቦታዎች እየተደረጉ ያሉ ጥንቃቄዎችም በይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝን ኅብረተሰቡን አስተባብሮ በባለሞያዎች ምክር መሠረት ለመከላከል መቻል፤ ከመከላከል ያለፈ ነገር ሲመጣ ለማከም የሚያስችሉ ዐቅሞችን ማዳበር እንዲሁም የከፋው ነገር ከመጣም አስቀድሞ በመዘጋጀት እንደየ አስፈላጊነቱ ተገቢ ውሳኔዎችን እያሳለፈ መሄድ የሚል መርህ ዘርግቶ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም