የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየሰሩ መሆኑን የአርባምንጭና ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች ገለፁ

118

አርባምንጭ/ሚዛን፤ ሚያዝያ 2/2012 (ኢዜአ) አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአከባቢውን ማህበረሰብ ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል 10 ሚሊዮን ብር  በጀት ሲመድብ፤ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ለኢዜአ እንዳሉት በአገሪቱ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመምጣቱ ስርጭቱ እንዳይሰፋ የመከላከል ስራ የሁሉም አካላት ድርሻ መሆን ይገበዋል።

ዩኒቨርሲቲው የንጽህና መጠበቂያ ለማምረት፣ ለግንዛቤ ፈጠራ፣ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎትና ሌሎች ስርጭቱን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን ለማስፈጸም 10 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ካሉት 6 ካምፓሶች መካከል የግብርና ሳይንስ ፋኩሊቲ ኩልፎ ካምፓስን ለለይቶ ማከሚያና ማቆያ እንዲውል መወሰኑን አስታውቀዋል።

አርባ ምንጭ ከተማ የቱሪስት መዳረሻ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለቫይረሱ ተጋላጭ በመሆኑ ለከተማውና በዙሪያው ለሚገኙ ወረዳዎች ማህበረሰብ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።  

ዩኒቨርሲቲው በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ለሚገኘው ጊዜያዊ ማቆያ የሚያገለግል 30 ፍራሾችና አንድ መቶ አንሶላዎች ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ለማምረት አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከቤንች ሸኮና ምዕራብ ዞኖች ለተውጣጡ ከ200 ለሚበልጡ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን የዩኒቨርሲቲው ተወካይ ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመዲን ሙስጠፋ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ጎዳና ተዳዳሪዎች ና አቅመ ደካማ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑና ጉዳት እንዳይደርስባቸው አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት በመከላከል ስራው ላይ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር በማምረት ማሰራጨት መጀመሩንና ለለይቶ ማከሚያና ማቆያ እንዲውሉ በሚዛንና ቴፒ የሚገኙ ጊቢዎቹን ዝግጁ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም