የሚወራው ገቢራዊ ካልሆነ ለምን?

59

የሰራው ወርቁ (ኢዜአ)


የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ 19) እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በታህሳስ 2019 በቻይናዋ ውሃን ከተማ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ተጠቂ አድርጓል፤ ሙሉ በሙሉ ከበሽታው ያገገሙት በርካቶች ቢሆኑም ከ89 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።

በኢትዮጵያም በሽታው ከተከሰተበት ከመጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁኗ ሰዓት ድረስ 56 ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው አራት ከበሽታው አገግመዋል። ሁለት ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል። ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ በከፋ ሁኔታ እያጠቃቸው ካሉት አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ስፔንና ታላቋ ብሪታኒያ አንጻር ዝቅተኛ የጤና መሰረተ ልማት ያለባት አገር መሆኗ ሃቅ ነው።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመከላከል የተሻለው አማራጭ በህክምና ባለሙያዎች፣ በባለስልጣናትና በታዋቂ ግለሰቦች ዘወትር የሚለፈፈው የቅድመ ጥንቃቄ መንገድ ነው። አካላዊ ርቀትን ቢያንስ በሁለት የአዋቂ ርምጃ ርቆ መጓዝ፤ እጅን በተደጋጋሚ በውሃና ሳሙና መታጠብ፤ አለመጨባበጥ፤ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ አለመሄድ (ጭራሹን አለመሰብሰብ) ሲያስሉና ሲያስነጥሱ ፊትን ዞሮ በክንድ ማፈን የሚሉት ሁሌም በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚነገሩ እንዲያውም በሰዎች ዘንድ የተለመዱ ሆነዋል፤ ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ግን ትዝብታችንን እናካፍላችሁ።

ከ700 በላይ አባላት ያሉት ብሩህ ተስፋ የታክሲ ባለንብረቶች ማህበር 400 ለሚሆኑ የታክሲ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች አልኮል፣ የእጅ ጓንትና የአፍ መሸፈኛ ማስክ ለመስጠት ከረፋዱ 4:00 አካባቢ ጦር ሃይሎች ተርሚናል ከሚባለው ቦታ ቀጠሮ ይዟል። በሰዓቱና በቦታው የማህበሩን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ክፍሌ አገኘናቸው።

400 ለሚሆኑ የታክሲ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች (200 አሽከርካሪዎችና 200 ረዳቶች) ባለአንድ ሊትር አልኮል ለሁለት፣ ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ማስክ፤ እንዲሁም ለረዳቶች ብቻ ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የእጅ ጓንት እንደሚከፋፈል አስረዱን። በቀጣይም ለአሽከርካሪዎችና ረዳቶች ብሎም ለተሳፋሪዎች ደህንነት ሲባል ይሄ ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑን አስረግጠው ነገሩን።

አሽከርካሪዎችና ረዳቶችንም እንዲሁ ጠየቅናቸው፤ ''እኛ ሃላፊነት ስለሚሰማን መንግስት ያወጣውን መመሪያ አክብረን እንሰራለን'' አሉ። ተሳፋሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ እንዴት መቀመጥ እንዳለባቸው ማስረዳት ቀዳሚ ስራቸው መሆኑን ገለጹልን፤ ለአቅመ ደካሞች ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ እገዛ እናደርጋለንም አሉን። ከመንግስት ቅጣት ይደርስብናል ብለን ሳይሆን በሽታውን መከላከል የእኛም ድርሻ ስለሆነ ትርፍ መጫን "በአፍንጫችን ይውጣ" እያሉ ሲምሉ ሲገዘቱ ታዘብን። "የራሳችንን አካላዊ ርቀት በመጠበቅ ተሳፋሪዎችን አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲቀመጡ እናደርጋለን" ብለው ነገሩን።

ወዲያውኑ ይሄው ለእደላ የተዘጋጀውን አልኮል፣ የእጅ ጓንትና የፊት መሸፈኛ ማከፋፈል እንዲጀመር ከአንዲት የፖሊስ መኪና ውስጥ ያለ ሰው በማይክራፎን ትዕዛዝ ሰጡ። "ይሄንን አስከፊ በሽታ ለመከላከል አካላዊ ርቀታቸውን እንደጠበቁ ይከፋፈል" እያሉ በማይክራፎን አሁንም እየተናገሩ ነው። በዚህ ወቅት በግምት ከመቶ የሚበልጡ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች እንዲሁም የሚሰጠውን ቁሳቁስ ማየት የፈለጉ በአደባበዩ አካባቢ የተኮለኮሉ ሰዎች መሰብሰብ ጀመሩ። እንዲያ በወሬ ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ስለ አካላዊ ርቀት የነገሩንን ረስተው ተቃቅፈው ቆሙ፤ ተሰለፉ ሲባሉም እኔ እቀድም እኔ እቀድም ሲራኮቱ "ሁለት የአዋቂ ርምጃ" የሚለውን ወደ ትግል ቀየሩት። በጣም የሚገርመው መኪና ውስጥ ሆኖ እባካችሁን አካላዊ ርቀታችሁን ጠብቁ እያለ በማይክራፎን ሲናገር የነበረው ሰውየ ራሱ ከመኪና ወርዶ መቀላቀሉ ነው።

በመጨረሻም የተፈጠረው ጥግግት እደላውን ለማከናወን አስጀጋሪ በመሆኑ ሁሉም በራሳቸው ታክሲ ውስጥ ገብተው እንዲከፋፈሉ ተደረገ። ሰው የማይተገብረውን ለምን ያወራል? ከተናገረ ለምን መተግበር ይሳነዋል?  ብዙ ማውራት ሃሳብ ለማመንጨት ያግዝ ይሆናል፤ ነገር ግን ሀሳቡስ ቢሆን ተግባራዊ ካልተደረገ ምን ይሰራል? ንግግራችንና ተግባራችን አንድ ይሁን፤ የማናደርገውን አንናገር፤ መናገር በተግባር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም