አይኤምኤፍ ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሰጠውን ብድር እጥፍ አደረገ

80

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2012 (ኢዜአ) የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ለአስቸኳይ ጊዜ የማበደር አቅሙን ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማድረጉን አስታወቀ።

ተቋሙ የማበደር አቅሙን ከፍ ያደረገው በኮሮቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንደሆነ በማኔጂንግ ዳይሬክተሯ በኩል ማሳወቁን ፋይናንሻል ታይምስ የዜና ምንጭ ዘግቧል።

ዳይሬክተሯ ክርስታሊና ጂኦርጂቫ አዲሱን የብድር አቅርቦት ዛሬ ይፋ ሲያደርጉ እንዳሉት፤ አገሮች የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በተወሰነ ደረጃ  ለማሳካት የአስቸኳይ ጊዜ የማበደር አቅሙን እጥፍ አድርጓል።

በቀጣይ የአለም ገበያ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች በወረርሽኙ ምክንያት በከፍተኛ ተጎጂዎች ናቸው።

ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሰጠውን ብድር እጥፍ ለማድረግ በገንዘብ ተቋሙ ቦርድ መጽደቁን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፤  ለርዋንዳ፣ ቶጎና ማዳጋስካር ብድር ለመስጠት በሂደት ላይ ካሉ አገሮች መካከል እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

የኮሮናቫይረስ በአለም ደረጃ በፍጥነት መስፋፋቱን ተከትሎ ከ90 በላይ አገሮች ለተቋሙ የብድር ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

''አለም በበሽታው ምክንያት የገባበት ቀውስ ማብቂያው መቼ እንደሆነ አይታወቅም'' ያሉት ዳይሬክተሯ፤ የ2020 የአለም ምጣኔ ሃብት እድገት በአሉታዊ መልኩ እንደሚቀጥል ጨምረዋል።

ሆኖም የምጣኔ ሃብት ቀውሱ ያደገና ገና በመምጣት ላይ ያለውን ምጣኔ ሃብት የሚጎዳ ቢሆንም ጠንካራ ኢኮኖሚ የሌላቸው አገሮች የበለጠ እንደሚጎዱ በአጽንኦት ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች እንዲሁም ለአለም ገበያ ማንሰራራት በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያስፈልግ በመሆኑ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋል።

አይኤምኤፍ የአለም አገሮች የኮሮናሻይረስ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት የሚፈጠረውን የገንዘብ እጥረት ከግምት በማስገባትሌሎች የብድር አማራጮችን ለማቅረብ እያሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም