ማህበሩ በዲላ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች የቀለብ እህል ድጋፍ አደረገ

117

ዲላ (ኢዜአ) ሚያዚያ 1/2012 በዲላ ከተማ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ 31 ለሚሆኑ አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች የቀለብ እህል ድጋፍ ማድረጉን የከተማዋ ጤና ስፖርት ማህበር ገለጸ።
የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ባምላኩ ዳምጠው ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን መከሰቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሁሉም ሰው ጎሮቤቱን ማየት እንዳለበት ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ምላሽ ለመስጠት የተደረገ ድጋፍ ነው ።

የማህበሩ አባላት ያላቸውን በማዋጣትና ሌሎችን በማስተባበር በከተማዋ ለሚገኙ 31 አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች የአንድ ወር ቀለብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በነፍስ ወከፍ 20  ግራም ዱቄት፣ ሶስት ኪሎ ግራም ሽሮ፣ ሁለት ሊትር ዘይት፣ ሽንኩርት፣ ሻማ እንዲሁም የግል ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ያካተተ ድጋፍ ተደርጓል ።

የማህበሩ አባላት ድጋፉን ቤት ለቤት ከማደላቸውም ባለፈ ከቤት እንዳይወጡና እጃቸውን ደጋግመው መታጠብ እንዲችሉ ግንዛቤ አስጨብጠዋል።

በቀጣይም 30 ለሚደርሱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ የልየታ ስራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የሰዎች እንቅስቃሴ በመገደቡ እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ሰርተው ለመብላት መቸገረቸውን ተናግረዋል።

በጣም አስፈላጊ በሆነ ወቅት የምግብ ድጋፍ በማግኘታቸው የተሰማቸውን ድስታ ገልጸው ድጋፉን ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል

ወይዘሮ ብርቄ ተሰማ የተባሉ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ኑሮአቸውን በየሰው ቤት ተዘዋውረው በቀን ስራ እንደሚመሩ ይናገራሉ።

በሽታው በሀገራችን መከሰቱን ተከትሎ የሰዎች እንቅስቃሴ በመገደቡ ተዘዋውረው መስራት ባለመቻላቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሮአቸው ችግር ውስጥ መግባቱን አስረድተዋል።

በዚህ ወቅት ድጋፍ በማግኝታቸው የተሰማቸውን ድስታ ገልጸው ድጋፉን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ትግሉ በቀለ በበኩላቸው በከተማው የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የሀብት አፈላላጊ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የተለያዩ ድጋፎችን እያሰባሰበ ነው።

በከተማው ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች የመንግስትን ጥሪ አክብረው የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል ።

የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እንቅስቃሴዎች መገደባቸውን ተከትሎ የእለት ጉርሳቸውን በቀን ስራ ተሰማርተ የሚያገኙ ወገኖች ለችግር እንዳይዳረጉ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

በዚህ ረገድ የዲላ ከተማ ጤና ስፖርት ማህበር ያደረገው ድጋፍ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል ሲሆን ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም