ወረርሽኙን ለመከላከል የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የጤና ባለሙያዎች አስታወቁ

93

ሐዋሳ (ኢዜአ) ሚያዚያ 1/2012  የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በሐዋሳ ከተማ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች አስታወቁ።

የጤና ባለሙያዎቹ ዛሬ በሐዋሳ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የእግር ጉዞ በማድረግ  ስለበሽታው አስከፊነትና መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ዙሪያ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከጤና ባለሙያዎቹ መካከል በሀዋሳ ከተማ አዳሬ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ዶክተር ገላጋይ ዘውዴ በሰጡት አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ  እንደኛ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ከተስፋፋ ሊያስከትል የሚችለው ቀውስ ከፍተኛ ነው።

የኛ አቅም አስቀድሞ መከላከል ላይ በትኩረት መስራት ነው ያሉት ዶክተር ገላጋይ የከተማው ህብረተሰብ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ በማሰብ የእግር ጉዞ ፕሮግራም አዘጋጅተን የጥንቃቄ መልዕክቶችን አስተላልፈናል ብለዋል ።

እንዲህ አይነት ወረርሽኝ ሲከሰት በየትኛውም የህክምና ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ያለ ልዩነት መረባረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው ሁኔታው እየከፋ ከመጣም አስፈላጊውን ሙያዊ ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በሽታው እስካሁን በሀዋሳ ከተማ አልተገኘም ማለት የተጠቃ ሰው የለም ብሎ ለመደምደም የሚያስችል አይደለም ያሉት ዶክተር ገላጋይ በከተማዋ እየተስተዋለ ያለው መዘናጋት ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከወዲሁ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባው አሳስበዋል ።

በዚሁ ሆስፒታል የሚያገለግሉት ሲስተር ምርትነሽ ገነሞ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ባደጉ ሀገራት ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት አንፃር በሀገራችን እንዳይስፋፋ ቅድሚያ በመከላከሉ ስራ  ላይ መረባረብ ይገባል።

 ይህንን ወረርሽኝ መከላከል ውዴታችን ብቻ ሳይሆን ሙያዊ ግዴታችን ነው ያሉት ሲስተር ምርትነሽ ሁኔታው ገፍቶ ከመጣ በየትኛውም ሥፍራ የሚጠበቅብንን አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተናል ብለዋል ።

በከተማዋ የአላሙራ ጤና ጣቢያ ኃላፊ ሲሳይ ቢሻሮ በበኩላቸው በተቋማቸው ለተገልጋዮች አስፈላጊውን የጥንቃቄ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ ባሻገር የሙቀት መለኪያ መሳሪያ በመጠቀም የመለካትና አጠራጣሪ ሁሌታዎች ሲያጋጥሙ ለተጨማሪ ምርመራ የመለየት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን  ተናግረዋል ።

እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የተቋሙ ባለሙያዎች ስርጭቱ የሚስፋፋ ከሆነ በሙሉ አቅማቸው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለመስጠት እንደሚረባረቡ አስታውቀዋል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ የከተማዋን ከንቲባ ወክለው የተገኙት አቶ አስፋው ጎኔሶ እንዳሉት የጤና ባለሙያዎቹ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ቁርጠኝነታቸውን በማሳየታቸው ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎች ወረርሽኙን ለመከላከል ግንባር ቀደም ተሰላፊ ናቸው ያሉት አቶ አስፋው ሆኖም በሚያከናውኑት ህዝብን የመታደግ ሥራ ውስጥ ለራሳቸውም ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

ህብረተሰቡም ከጤና ባለሙያዎችና ከመንግስት አካላት እንዲሁም ከሐይማኖት አባቶች እየተላለፉ ያሉትን የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተቀብሎ በመተግበር ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም