ኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ሕይወቱ ያለፈ ሰው አስከሬን ወደ አገር እንዳይገባ አገደች

51

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2012 (ኢዜአ) ከየትኛውም የዓለም ክፍል በኮቪድ 19 ሕይወቱ ያለፈ ሰው አስከሬን ወደ አገር ቤት እንዳይገባ ከዛሬ ጅምሮ መታገዱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ለአቪዬሽን ባለስልጣን ባስታወቀው መሰረት አገዳው ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ተላልፏል።

በዚሁ መሰረት ባለስልጣኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ወደ ኢትዮጵያ ለሚበሩ 14 አየር መንገዶች የክልከላውን ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ይህን አሰራር የጣሰ በዘርፉ የተሰማራ አካል ሃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑንና ቅጣትም እንደሚጠብቀው ባለስልጣኑ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ለአቬዬሽኑ የላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው ቫይረሱ ባህሪውን የሚቀያይር መሆኑና ገና በጥናት ያልተረጋገጡ ነገሮች ያሉት መሆኑን ጠቅሶ በቫይረሱ የሞተን ሰው አስከሬን ማጓጓዝ የበሽታው መተላለፊያ ሊሆን ይችላል ብሏል።

በመሆኑም ሕብረተሰቡ ከዚህ አስከፊ በሽታ ይጠበቅ ዘንድ አስከሬን ከየትኛውም አገር ወደ ኢትዮጵያ ማጓጓዝ ሊቆም ይገባል ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም