በድሬዳዋ ተቋርጦ የነበረው የታክሲ አገልግሎት ዛሬ ጀመረ

66

ድሬዳዋ ሚያዚያ 1/2012(ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር ተቋርጦ የነበረው የታክሲ  አገልግሎት ዛሬ በከፊል መጀመሩን የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ  አስታወቀ።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ  ኃላፊ   ሰአዳ  አዋሌ  ዛሬ  ለኢዜአ  እንዳስታወቁት  የኮሮና   ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ተቋርጦ የነበረው የከተማ ታክሲ አገልግሎት ዛሬ በከፊል ሥራ   ጀምሯል፡፡

በአስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ መሰረት ዛሬ አገልግሎቱ መጀመሩ የተከሰተውን ማህበራዊ  ችግር ለማቃለል ያግዛል ብለዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የሰሌዳ ቁጥራቸው ጎዶሎ ቁጠር የሆኑት  ታክሲዎች  አገልግሎት  መስጠት  የጀመሩ  ሲሆን  ቀጣዩን  ቀን ደግሞ ሰሌዳቸው ሙሉ ቁጥር የሆኑት እንዲሰሩ  ይደረጋል ።

አብዛኛው የመንግስት መስሪያ ቤቶችና  የተቋማት  ሠራተኞች  እቤት  በመዋላቸውና   ትምህርት ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ሳቢያ አገልግሎቱ በከፊል እንዲጀምር መደረጉን ነው ወይዘሮ ሰአዳ ያስረዱት፡፡

ነገር ግን መጨናነቅ  ከተከሰተና  ለኮሮና ቫይረስ መሰራጨት መንስኤ የሚሆኑ ክስተቶች ከተስተዋለ ችግሩን ለመፍታት ሁሉም እንዲሰሩ እንደሚደረግ ተናገረዋል፡፡

ታክሲዎቹ የቫይረሱን ስርጭት ለመከልከል የመጫን አቅማቸውን በግማሽ ቀንሰው  እንዲሰሩ መወሰኑን ተናግረው ይህን መመሪያ በተላለፉ ላይ አስፈላጊው እርምጃ  እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡም አካላዊ ርቀቱን በመጠበቅና የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ኃላፊነቱን  በመወጣት አገልግሎቱን እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል ትራንስፖርት  መጀመሩ  ማህበራዊ  ችግራቸውን  ያቀለለው  ቢሆንም   ተጠቃሚው የኮሮና  ቫይረስን  የመከላከል  ኃላፊነቱን  ሊወጣ  እንደሚገባ  አስተያየታቸው ለኢዜአ የሰጡ የድሬ ዳዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የታክሲ ተጠቃዎቹ እንደተናገሩት የታክሲ አገልግሎቱ መጀመሩ የተፈጠረባቸውን የኑሮ ጫናና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በከፊል እንደሚያሻሽለው ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ራዚያ መሐመድ በሰጡት አስተያየት ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ ከሣቢያን እስከ  ቀፊራ በታክሲ እየተመላለሱ አትክልት በመሸጥ ይተዳደሩ እንደነበር አስታውሰው የታክሲ  አገልግሎት በመቋረጡ በኑሯቸው ላይ ጫና መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡

አሁን ግን ‹‹የታክሲ አገልግሎቱ መጀመሩ ለኔና እንደኔ በዕለት ሥራ ለሚተዳደሩ ሰዎች ትልቅ እፎይታ ነው ›› ብለዋል፡፡

የታክሲ አገልግሎቱ መጀመሩ ጥሩ ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበረው ዋጋ እጥፍ እንድንከፍል መደረጉ አግባብ አይደለም ያሉት ደግሞ አቶ ብርሃኑ ወርቅነህ ናቸው፡፡

‹‹በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ሰው የሚያስከፍለውን ሲቀንስ የታክሲ ክፍያ መጨመሩ ትክክል  ባለመሆኑ ስተዳደሩ ውሳኔውን መልሶ እንዲፈትሽ ጠይቀዋል ።

አቶ ተዘራ ገብረህይወት የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ታክሲ ለማግኘት ተሳፋሪው የሚያደርገው ንክኪ ለኮሮና ቫይረስ መሰራጨት መንስኤ ስለሚሆን ከወዲሁ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል ።

የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የለውጥና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ  እንዳሉት የአስተዳደሩ ካቢኔ ያስተላለፈውን ውሳኔና መመሪያ በትክክል እንዲተገብር  የትራፊክ ፖሊስ ቁጥጥሩን አጠናክሯል ፡፡

ህብረተሰቡ መመሪያውን የተላለፉ ተሸከርካሪዎች ሲያጋመው ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀው ነዋሪውም አካላዊ ርቀቱን በመጠበቅ እራሱን ከበሽታው እንዲከላከል መልእክት አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም