ተቋማቱ አፍሪካን ወደ አንድ ቤተሰብ እያቀራረበ ላለው ስፖርት መጠናከር ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

56
መቀሌ 25/2010 አፍሪካን ወደ አንድ ቤተሰብ እያቀራረበ ያለው የስፖርት ዘርፍ ይበልጥ እንዲጠናከር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ አስታወቁ። ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌጤ 9ኛው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ውድድር በመቀሌ ከተማ በሚገኘው ትግራይ ስታዲየም ትናንት ሲጀመር እንደገለፁት በአፍሪካ በተለያዩ ጊዜያት እየተካሄዱ ያሉ የስፖርት ውድድሮች ህዝቦቿ ይበልጥ እንዲቀራረቡ እያገዙ ነው። "በስፖርት ዘርፍ እየተካሄዱ ያሉ የውድድር ሂደቶችና ምርምርና ጥናቶች ዘርፉን ከማጎልበታቸው ባለፈ አፍሪካውያንን እንደ አንድ ቤተሰብ በማሰባሰብ አስተዋጾ እያደረጉ ነው" ብለዋል። ተቋማቱ በዘርፉ ለሚያከናውኗቸው ስራዎች መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው " የኢትዮጵያ የስልጣኔ ማማ ወደሆነችው ትግራይ እንኳን ደህና መጣችሁ" በማለት ለተሳታፊዎች አቀባበል አድርገዋል፡፡ "የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ቅኝ መገዛትን ስናስታውስ የአድዋን የነጻነት ታሪክ ማንሳታችን አይቀሬ መሆኑ ለውድድሩ የበለጠ ድምቀት ይሰጠዋል" ብለዋል። "የውድድሩ ተሳታፊዎች ወደ ሁለተኛ ቤታቸው እንደመጡ አድርገው ሊቆጥሩት ይገባል" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በቆይታቸው ከውድድር በተጨማሪ  በመቀሌ ከተማ ያለውን የሰማዕታት ኃውልትና የአፄ ዮሐንስ ሙዚየምን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ታሪካዊ መስህቦችን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል። የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶክተር ማሉምቤት ራሌዝ በአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የስፖርት ውደድሮች አፍሪካያዊነታችንን የሚያጎከለብቱ ስለመሆናቸው በወጣቶች ዘንድ ግንዘቤ ሊያዝ እንደሚገባ ተናግረዋል። በውድድሩ መክፈቻ ስነ ስርአት ላይ  ከ18 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ተካፋዮች የመጡባቸውን ሀገራትና ዩኒቨርሲቲዎች ስም ለስፖርት ታዳሚው አስተዋውቀዋል። በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበረሰብና አመራሮች ተገኝተዋል። ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ውድድር በ10 የስፖርት አይነቶች ከ900 በላይ ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም