በሐዋሳ ከተማ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሀብት የማሰባሰብ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው

53

ሐዋሳ (ኢዜአ) ሚያዚያ 1/2012 በሐዋሳ ከተማ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ባለሀብቶችንና ተቋማትን በማስተባበር ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የከተማው አስተዳደሩ አስታወቀ። 

በከተማው ትናንት ማምሻውን በተካሄደ የሐብት ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የሐዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እንደገለፁት የበሽታውን ወረርሽኝ አስቀድሞ ለመከላከል ሁለንተናዊ ዝግጅት ያስፈልጋል።

በዚህ ረገድ ከተማ አስተዳደሩ የቫይረሱን ስርጭት መከላከያ ዘዴዎችንና ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች አስመልክቶ ለህብረተሰቡ በተለያዩ ዘዴዎች ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አወያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ ስርጭቱን ለመከላከል እንዲቻል የሀብት ማሰባሰብ እንዲሁም ለለይቶ ማቆያና ለህክምና መስጫ አገልግሎት የሚሆኑ ስፍራዎችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ነው።

ሁኔታው እየከፋ ከሄደ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ እነሱን ለመታደግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ከወዲሁ እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ስኬት ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባው የገለጹት ምክትል ከንቲባው የከተማ አስተዳደሩን ጥሪ በመቀበል በገንዘብና በአይነት ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ባለሀብቶችንና ተቋማትን አመስግነዋል።

የሀዋሳ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ኃላፊና የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አፈወርቅ አለማየሁ በበኩላቸው በከተማዋ እየተካሄደ ባለው ሀብት የማሰባሰብ እንቅስቃሴ ባለሀብቶች ፣ የእምነት ተቋዋማት፣የሙያና ሌሎችም ማህበራት እየተሳተፉ ነው።

ትናንት በተካሄደው መርሃ ግብር ብቻ  ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን እስከ አሁን በጥሬ ገንዘብ የተገኘው ድጋፍ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በአይነት ደግሞ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተገኝቷል።

በድጋፉ ከተሳተፉት መካከል የታቦር ሴራሚክስ ውጤቶች አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ዩኬ በሰጡት አስተያየት ማህበሩ በሽታውን ለመከላከል ስራ አንድ ሚሊዮን ብር ሰጥቷል።

አሁን ላይ የመከላከል ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆኑም ሁኔታዎች ነገ ወዴት እንደሚያመሩ ስለማይታወቅ ለቅድመ ዝግጅት ሥራው ማህበሩ የአቅሙን እገዛ ለማድረግ መነሳሳቱን ተናግረዋል። 

ከዕምነት ተቋማት መካከል በኢትዮጵያ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን የማዕከላዊ ደቡብ ኢትዮጵያ ሲኖዶስ 100 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የሲኖዶሱ ፕሬዝዳንት አቶ ኢያሱ ጣጊቾ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መመሪያዎችን እየተገበርን ሁላችንም  በሽታው ከሀገራችንና ከዓለማችን ይወገድ ዘንድ በንስሀ ውስጥ ሆነን በርትተን ልንፀልይ ይገባል ብለዋል።

ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ኢያሱ ሁሉም ሰው በልቶ ለማደር የሚቸገሩ ወገኖችን ማሰብና መደገፍ ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም