ኢትዮጵያ የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያን ልትተገብር ነው

66
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 ኢትዮጵያ የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያን ሕጋዊና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመተግበር እየተዘጋጀች መሆኑን የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት መርሃ ግብር (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ጋር በመሆን የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያን አስመልክቶ በተካሔደው ጥናት ዙሪያ  የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል። ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ቅንጅታዊ አሰራርን የሚያጎለብትና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የሚያመች ነው። የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ የአካባቢ ጥበቃ ስራው ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርግና ከዘርፉ መጠቀም ያለበት አካል ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑንም ነው ያብራሩት። የስርዓተ ምህዳር ክፍያ አንዱ ለሚያከናውነው የአካባቢ ጥበቃ ስራ በሌላ ቦታ ሆኖ ጥቅም እያገኘ ያለው አካል ክፍያ እንዲፈጽም የሚያስገድድ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የብዝሃ ህይወት ማካተቻና ማትጊያ መርሃ ግብር ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ አብደታ ደበላ እንዳሉት ደግሞ የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ በፍጥነት እየተመናመነ የመጣውን የአካባቢ መራቆት ችግር ያቃልለዋል። የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚነት፣ እድገቷን ለመደገፍና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጎልበትም የጎላ እስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የገለጹት። የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ከገንዘብ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ ጉዳይ አንጻር እጅግ ውጤታማ መሆኑን እስካሁን የተካሄደው የአዋጭነት ጥናት ማረጋገጡንም ገልጸዋል። በተለይም ከውኃ አካላት ክፍያ ጋር በተያያዘ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ተጠቃሚዎቹ የሚከፍሉበትን ስርዓት ለመዘርጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን  የሚኒስቴሩ ተወካይ አቶ ክፍሌ አለማየሁ ተናግረዋል። አቶ ክፍሌ እንዳብራሩት እስካሁን ባለው ሁኔታ ከተሞች አካባቢ የውኃ አገልግሎት ክፍያ ቢኖርም  በሰፊው ጥቅም ላይ ለሚውሉ ውኃና የውኃ አካላት ተገቢው ክፍያ እየተፈጸመ አይደለም። በቀጣይ ግን ከውኃ አካላት ተጠቃሚ የሆኑ ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚደረግ መሆኑን አብራርተዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስ ሉዊስ ቻምበርሊን በበኩላቸው አሰራሩ ኢትዮጵያ ከስነ ምህዳሯ የበለጠ  ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላታል ብለዋል። አሰራሩ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ኖሯቸው ስርዓተ ምህዳርን የሚንከባከቡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድግ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት። የክፍያ ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንደሚያስፍልግም አመልክተዋል። በውይይት መድረኩ  የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ አጠቃላይ ሁኔታና አዋጭነት፣ መልካም አጋጣሚና ተግዳሮቶቹን በተመለከተ ገለጻ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም