የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የከተማዋን ነዋሪዎች እየጠቀመ መሆኑ ተገለጸ

53
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ለሞጆ ከተማ ዕድገትና ነዋሪዎች ዘርፈ-ብዙ ጥቅም እያስገኘ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ። ከተማዋ ከሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ባገኘችው የ35 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነች መሆኗን ተገልጿል። 'ሞጆ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ባላት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ስትራቴጂካዊና የዝውውር ከተማ ናት' ያሉት በከተማ አስተዳደሩ የፓለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ተክለሃና፤ በዚህም ከተማዋ ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆኗን አንስተዋል። በከተማዋ የተገነባው የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናልም ለከተማዋ ነዋሪዎች በስራ ዕድል ፈጠራ ካስገኘው አስተዋጽኦ ባሻገር፣ ለማህበራዊ አገልግሎት በሰጠው የ35 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናውን  የህብረተሰቡን ችግሮች ማስተካከሉን አንስተዋል። ደረቅ ወደቡ የለገሰው ድጋፍ ተግባራዊ እንዲሆን ከህብረተሰቡና ከከተማዋ ምክር ቤት የተወጣጣ ኮሚቴ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ እስካሁንም የገልባጭ መኪና፣ ሎደር፣ የደረቅ ቆሻሻ ማንሻዎች ተገዝተው ስራ ላይ መዋላቸውን ጠቅሰዋል። ከተማ አስተዳደሩ ከደረቅ ወደብና ተርሚናሉ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳለው ገልጸው በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ስራ ያላገኙ የከተማዋ ወጣቶች የስልጠናና የስራ ዕድሎች እንዲፈጠርላቸው በተደረገው ስምምነት መሰረት ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም