አለም አቀፍ ኩባንያዎች የፍጆታ ሸቀጦችን ወደ አገር በማስገባት ሂደት እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አለም አቀፍ ኩባንያዎች የፍጆታ ሸቀጦችን ወደ አገር በማስገባት ሂደት እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2012( ኢዜአ) በአገር ውስጥ የፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰት አለም አቀፍ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከአሁን በፊት መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ከውጭ የማስገባት የንግድ ፈቃድ ያላቸው የአገር ውስጥ ባለሃብቶችና መንግስት ሲሆኑ ለውጭ ኩባንያዎች የተፈቀደው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ተከትሎ እጥረት እንዳይከሰት በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የውጭ ኩባንያዎቹ ከሚያዚያ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለ15 ቀናት የፍላጎት ማሳወቂያ ሰነድ በኢ-ሜል እንዲልኩ ይፋ ተደርጓል።
ከውጭ ገቢ የሚሆኑት ምርቶች ስንዴ፣ የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ ሩዝ ሲሆኑ ዝርዝር መረጃው በሚኒስቴሩ ድረ-ገፅ፣ በኢትዮጵያን ሄራልድና በሪፖርተር ጋዜጦች እንደሚወጣም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ወኪል ያላቸው ኩባንያዎች በአሁኑ ወቅት መመዝገብ መጀመራቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በውጭ የሚገኙ ኩባንያዎች በኢ-ሜል ማሳወቅ እንደሚችሉም አመልክተዋል።
ከ15 ቀናት በኋላ ወደ ስራ የሚገቡት ተለይተው በገቢ ንግዱ ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ መሆኑን ተናግረው፤ እንዲሳተፉ የሚፈቀድላቸው ኩባንያዎች ህጋዊ መሰረት ያላቸውና የሂሳብ እንቅስቃሴያቸው ጤናማ መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አቶ ወንድሙ ገልጸዋል።
የውጭ ኩባንያዎች በዚህ ንግድ ላይ መሰማራታቸው በአገር ውስጥ ያለውን አቅርቦት ከማሳደግ ባለፈ መንግስት ምርቶቹን ለመግዛት የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሬ እንደሚቀንስም ነው የገለጹት።
ኩባንያዎቹ ደረጃውን የጠበቀ የፍጆታ እቃ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የሚደረግና መንግስት በሚያወጣው የዋጋ ተመን መሰረት ለሽያጭ የማቅረብ ስምምነትም ይፈርማሉ ተብሏል።
ጨረታው ለአንድ አመት የሚቆይ ሲሆን ስንዴ፣ የምግብ ዘይት፣ ስኳርና ሩዝ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።